Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ኦሞ ዞን በግጦሽ መሬት ምክንያት ተፈጥሮ የነበረው ግጭት በእርቅ ተፈታ

አዲስ አበባ፣ጥር 16፣2014 (ኤፍ ቢሲ) በደቡብ ኦሞ ዞን በኛንጋቶም፣ ካራ፣ ሐመርና በኮይጉ ህዝቦች መካከል በግጦሽና በእርሻ መሬት ምክንያት ተፈጥሮ የነበረው ግጭት በእርቀ ሰላም መቋጨቱን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።

በደቡብ ኦሞ ዞን በሚገኙ ህዝቦች መካከል ለዓመታት የዘለቀውን አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የእርቀ ሰላም ኮንፍራንስ በዛሬው እለት በሐመር ወረዳ ካራዱስ ቀበሌ ተካሂዷል ።

በእርቀ ሰላም ኮንፈረንሱ ላይ የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ንጋቱ ዳንሳ እንደገለጹት፥ የኛንጋቶም፣ ካራ፣ ሐመር እና ኮይጉ ህዝቦች በባህል፣ በእምነት፣ በማህበራዊ አኗኗር እና በጋብቻ የተሳሰሩት ናቸው ።

በተለያዩ ጊዜያት በግጦሽ መሬትና በወንዝ ዳርቻ ያለን መሬት ለእርሻ ለመጠቀም የሚደረግ ግጭት፣ የከብቶች ስርቆትና ዝርፊያ እንደሚፈጸም ጠቅሰዋል።

እንዲህ ዓይነት ጊዜ የሚወስድና ያልተገባ ዋጋ እያስከፈለ ያለ አለመግባባት ተገቢነት የለሌው መሆኑን የጠቀሱት ዋና አስተዳዳሪው የአካባቢው ነዋሪዎችን የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት የአካባቢዎቹን ማህበረሰብ የልማት ተጠቃሚ ለማድርግ እየተሰራ መሆኑን ነው ያመለከቱት።

የደቡብ ክልል አርብቶ አደር ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሎሬ ካኩታ በበኩላቸው፥ ግጭቶቹ የአከባቢውን ልማት እየጎዱ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረቱና ዘላቂ ሰላምን ማስፈን የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ተጠናክረው መሰራት እንዳለባቸው ነው ያሳሰቡት።

እርቀ ሰላሙን ካመቻቹት መካከል የጂንካ የህይወት ተስፋ ዓለም አቀፍ ቤተክርስቲያን አገልጋይና የኦሞ ቻየልድ ፋውንዴሽን መስራች አቶ ላሌ ላቡኩ”የተረጋጋችና ለጠላት የማትበገር ሀገር ለመገንባት የውስጥ ሰላምን መጠበቅ አስፈላጊ ነው” ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የሀገር ሽማግሌዎች በበኩላቸው በእርቀ ሰላም ኮንፈርንሱ የተገኘውን ሰላም ለማስቀጠል ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

”በህዝቦች መካከል ግጭት እንዲከሰት የተለያዩ ወንጀሎች የሚፈፅሙ አካላትን ለህግ አጋልጠን በመስጠት የህዝብ ለህዝብ ግኑኝነታችንን ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሃላፊነታችንን እንወጣለን” ብለዋል።

በእዕርቀ ሰላም ኮንፈርሱ የተሳተፉት የሐመር፣ የኛንጋቶም ፣ የካራ እና የኮይጉ ህዝቦች ተወካዮች በቀጣይ አለመግባባቶችን በውይይት ለመፍታት፣ የተፈጥሮ ሀብቶቻቸውን በጋራ ለመጠቀም እና ለአከባቢያቸው ሰላም ዘብ ለመቆም ቃለ መሃላ በመፈፀም ለዓመታት በመካከላቸው የተፈጠረውን ቂምና ቁርሾ በእርቅ ቋጭተዋል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.