Fana: At a Speed of Life!

ሀገር አቀፍ የአርብቶ አደሮች ቀን በአዳማ ከተማ እየተከበረ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) 18ኛው የኢትዮጵያ የአርብቶ አደሮች ቀን በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ እየተከበረ ነው፡፡

“የአርብቶ አደሩ ልማት ለሀገራዊ ብልፅግና” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ባለው 18ኛው የአርብቶ አደሮች ቀን ፥ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች፣ ከሁሉም የአገሪቱ ክፍል የሚመጡ የአርብቶ አደር ተወካዮች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ በአርብቶ አደር አካባቢ የሚገኙ ዩኒቨርስቲ ተወካዮች፣ ባለሀብቶችና ታዋቂ ግለሰቦች ተገኝተዋል፡፡

የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ አርብቶ አደሩ ለበርካታ ዓመታት ትኩረት ሳያገኙ ለችግር ተጋልጠዋል ያሉ ሲሆን ÷አሁን ግን ትኩረት ተሰጥቶ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ለዚህም ማሳያ በመስኖ ልማት ስንዴ ማምረት እንዲቻል እና አርብቶአደሩ ተጠቃሚ እንዲሆን የማድረግ ስራዎች ውጤት ማስገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

አርብቶአደሩን የልማት ተጠቃሚ ማድረግ እስካልተቻለ ድረስ ሀገራዊ እድገት ማሳካት እንደማይቻል የገለፁት አቶ ሽመልሽ አብዲሳ ፥ ለዚህ ደግሞ ሁሉም እገዛ ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

የቆላማ አካባቢ ምርምርና ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር እንድርያስ ጌታ በበኩላቸው ÷በ18ኛው የአርብቶአደሮች ቀን አርብቶአደሩ ያሉትን እምቅ ሀብቶች ለሀገር እድገት መጠቀም የሚችልበትን ሁኔታ ላይ ለመወያየት እድል የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ 17ሚሊየን የሚሆነው ህዝብ አርብቶአደር መሆኑን የገለፁት ሚኒስትር ዴኤታው ፥ የሀገርን ብልፅግና ለማረጋገጥ የዚህን ህዝብ የልማት ተጠቃሚነት ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

ለዚህም ሁሉም ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ኢትዮጵያ በታሪኳ አይታ የማታውቀው ችግር ገጥሟት ያለፈችበት ጊዜ መሆኑ 18ኛውን የአርብቶአደሮች ቀን ልዩ ያደርገዋል ያሉ ሲሆን ፥ በተደጋጋሚ የሚከሰተው ጎርፍና ድርቅ እንዲሁም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ብሎም የተፈጠረው ጦርነት በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኗል ነው ያሉት፡፡

ይሁንና የመስኖና የቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር መመስረቱ ይህን ችግሮችን ለማለፍ ይረዳናል ያሉ ሲሆን ፥ አርብቶአደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ ሁሉም በጋራ መስራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በመድረኩ የ2016 19ኛውን የአርብቶ አደሮች ቀን አዘጋጅ አፋር ክልል ሆኖ የአርማ ርክክብ አድርጓል፡፡
በታሪኩ ለገሰ

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.