ሃሰተኛ መታወቂያ ለጠላት አሳልፈው ለመስጠት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የተባሉ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ
አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጎንደር ከተማና ዙሪያ ወረዳ 314 ሀሰተኛ የቀበሌ መታወቂያ ለጠላት አሳልፈው ለመስጠት በድብቅ ሲያጓጉዙ የተገኙ የተባሉ ሁለት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ አስታወቀ፡፡
የጎንደር ከተማ ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግንኙነት ዋና ክፍል ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር እየሩስ አስማረ እንደገለጹት÷ ከተጠርጣሪዎቹ መካከል አንዱ ጥር 13 ቀን 2014 ዓም በተደረገ ክትትል በጎንደር ዙሪያ ወረዳ እንፍራዝ ከተማ 104 ሀሰተኛ መታወቂያዎችን ይዞ ተገኝቷል።
ሌላው ተጠርጣሪ ግለሰብም ጥር 14 ቀን 2014 ዓም በጎንደር ከተማ አዘዞ በሚገኘው መናኽሪያ አካባቢ 210 ሀሰተኛ መታወቂዎችን ይዞ መገኘቱን ተናግረዋል።
ከህብረተሰቡ የደረሰ ጥቆማ መሰረት በማድረግ በፀጥታ ሃይሉ በተደረገ ጥብቅ የደህንነት ክትትል ግለሰቦቹ ከነ ሀሰተኛ መታወቂያው እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን አስታውቀው፤በአጠቃላይ 314 ሀሰተኛ መታወቂያዎች በግለሰቦቹ እጅ መያዛቸውን አብራርተዋል።
ሀሰተኛ መታወቂያዎቹ በምእራብ ጎንደር ዞን በመተማ ወረዳ ሽኩራ በተባለ ቀበሌ ስም የተዘጋጁና በአካባቢው ለሚንቀሳቀሱ የጠላት ሃይሎች እጅ እንዲደርሱ ለማድረግ ታስቦ የነበረ መሆኑን ዋና ኢንስፔክተሯ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ተጠርጣሪ ግለሰቦቹ በህግ ጥላ ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ጠቁመው ሀሰተኛ መታወቂያዎቹ በባህር ዳር ከተማ በህገ-ወጥ መንገድ የታተሙ ስለ መሆናቸው መረጃዎች እንደሚያመለክቱ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!