እስራኤል የኢትዮጵያ መንግሥት ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሄደበት መንገድ የሚደገፍ መሆኑን ገለፀች
አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በእስራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር ረታ ዓለሙ ከእስራኤል ፕሬዚዳንት የውጭ ፖሊሲ አማካሪ ከሆኑት አምባሳደር ዚቪ ቪፒኒ ጋር በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ እንዲሁም በሁለትዮሽ ግኑኝነት ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱ አምባሳደር ረታ፥ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ በተለይም አሸባሪው ህወሃት በአፋርና አማራ ክልሎች የፈጸመውን ግፍና በደል አስረድተዋል።
አሁን ላይ መንግስት ለፖለቲካዊ መፍትሄ እና ለሰላም በሩን ክፍት በማድረግ፣ ሁሉን አቀፍ የውይይት መድረክ ለመጀመር ሁኔታዎች እንዲመቻቹ እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
ውይይቱ ሁሉን አካታች እንዲሆን ለማድረግና አገራዊ መግባባት ለመፍጠር ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን፣ ለዚህም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበውን አገራዊ ምክክር አዋጅ ማፅደቁን፣ የሚቋቋመው ኮሚሽን ለውይይት አጀንዳ የሆኑ ጉዳዮችን ለማቅረብ ሥልጣን የተሰጠው መሆኑን፣ በዚህም ውይይት የሚሳተፉት የፖለቲካ ድርጅቶች ለሰላማዊ ትግል የተዘጋጁ የኃይል አማራጭን የማይከተሉት መሆን እንደሚጠበቅባቸው አስረድተዋል።
አምባሳደር ዚቪ በበኩላቸው÷ እስራኤል እንደወዳጅ አገር የኢትዮጵያን ሰላምና መረጋጋት እንደምትፈልግ እና የኢትዮጵያ መንግስት አቋም እንደሚረዱ ገልፀው የኢትዮጵያ መንግሥት ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሄደበት መንገድ የሚደገፍ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የእስራኤል መንግስትም ኢትዮጵያን አስፈላጊ በሆነ መንገድ እንደሚደግፍ ማስታወቃቸውን ከእስራኤል የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!