የደብረ ብርሀን ከተማን ታሪክ እና ዕድገት የሚመጥን መዋቅራዊ ፕላን ለመስራት የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ
አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የደብረ ብርሀን ከተማን ታሪክ እና ዕድገት የሚመጥን የተቀናጀ መዋቅራዊ ፕላን ለመስራት የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ።
የደብረ ብርሀን ዩኒቨርሲቲ እና የደብረ ብርሀን ከተማ አስተዳደር ናቸው ስምምነቱን የፈጸሙት።
የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ንጉስ ታደሰና የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ካሳሁን እምቢአለ የስምምነት ፊርማውን ተፈራርመዋል።
ከተማዋ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ፍሰት ያላት እና ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር እየተመዘገበባት ነው ተብሏል፡፡
ወደ “ሪጂዮ ፓሊታንት” ከተማነት ያደገች በመሆኑ ከዚሁ ጋር የተመጣጠነ መዋቅራዊ ፕላን አስፈላጊ በመሆኑ ስምምነት መደረጉ ተገልጿል።
ዩኒቨርሲቲው ከከተማ አስተዳደሩና ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመሆን ወቅታዊና የከተማዋን ዕድገት የሚመጥን መዋቅራዊ ፕላን በአጭር ጊዜ አዘጋጅቶ እንደሚያቀርብ ተገልጿል።
ደብረ ብርሃን ከተማ በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና ከተማ ስትሆን፥ በዘጠኝ የከተማ ቀበሌዎች እና በአምስት የገጠር ንዑስ ቀበሌዎች የተከፋፈለችና አጠቃላይ የአስተዳደር ክልል የቆዳ ስፋቷ18 ሺህ ሄክታር መሆኑም ተመላክቷል፡፡
በቀጣይ ከአዲስ አበባ ወደ አሰብ ለሚደረገዉ የትራንስፖረት መስመር ተመራጭና ተጠቃሚ ትሆናለችም ነው የተባለው፡፡
ከተማዋ በአፄ ዘርዓ ያዕቆብ በመናገሻ ዋና ከተማነት በ1446ዓ.ም እንደተቆረቆረችም ይነገራል፡፡
በግርማ ነሲቡ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!