በሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልሎች የተከሰተውን ድርቅ ለመከላከል የተቀናጀ ጥረት ያስፈልጋል ተባለ
አዲስ አበባ፣ ጥር 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልሎች የተከሰተው ድቅር የከፋ ጉዳት ሳያደርስ ለመከላከል የተቀናጀ ጥረት እንደሚያስፈልግ የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ባለፉቱ ወራት በሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልሎች በተለለያዩ አካባቢዎች ዝናብ አለመጣሉን ተከትሎ በርካታ ዜጎች ለከፍተኛ የድርቅ አደጋ ተጋልጠዋል፡፡
በሶማሌ ክልል በተከሰተው ድርቅ ምክንያት አሁን ላይ 9 ዞኖች ለድርቅ አደጋ መጋለጣቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ፥ በዚህ ሳቢያም 2 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ ዜጎቸ እርዳታ ይፈልጋሉ ብለዋል፡፡
በክልሉ ለሚገኙ ተጎጂዎች ከባለፈው ግንቦት ወር እስከ መስከረም ድረስ 620 ሺህ ኩንታል የምግብ እህል እንዲሁም ከመስከረም እስከ ታህሳስ ወር 524 ሺህ 780 ኩንታል የምግብ እህል በዓለም የምግብ ፕሮግራም አማካኝነት መሰራጨቱን ተናግረዋል፡፡
በመንግስት በኩልም ከክልሉ በቀረበው መረጃ መሰረት ለ964 ሺህ 806 ዜጎች የሚሆን ሩዝ እና የተያዩ አልሚ ምግቦች ወደ አካባቢዎቹ መላካቸውን ነው ያመለከቱት፡፡
በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል ድርቅ በተከሰተባቸው ቦረና እና ጉጂ ዞኖች ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች አስፈላጊውን የምግብ እህል እርዳታ ለማዳረስ እየተሰራ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
በዚህም በቦረና ዞን ለሚገኙ ከ166 ሺህ በላይ ዜጎች በመንግስት ደረጃ በመጀመሪያ ዙር 14 ሺህ 760 ኩንታል ፣ በ2ኛ ዙር 9 ሺህ 351 ኩንታል እንዲሁም ተጨማሪ 17 ሺህ 281 ኩንታል የምግብ እህል መላኩን ተናግረዋል፡፡
በጉጂ ዞን ለሚገኙ 46 ሺህ 790 በድርቁ ለተጎዱ ዜጎችም 7 ሺህ 526 ኩንታል የምግብ እህል ወደ ስፍራው ተልኳል ነው ያሉት፡፡
በተጨማሪም አሁን ላይ በምስራቅ ባሌ በተከሰተው ድርቅ 251 ሺህ ዜጎች እርዳታ እንደሚፈልጉ ከክልሉ ጥያቄ መቅረቡን ጠቅሰው፥ ለእነዚህ ዜጎች ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የተከሰተው ድቅር የከፋ ችግር ሳያስከትል ለመከላከል ኮሚሽኑ በሁለቱ ክልሎች የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከል በማቋቋም አስፈላጊው ድጋፍ ለተጎጂዎች እንዲዳርስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል ዳይሬክተሩ፡፡
የተከሰተው ድርቅ የከፋ ችግር ሳያደርስ ለመከላከል የተቀናጀ ጥረት ይጠይቃል ያሉት ዳይሬክተሩ፥ ለዚህም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡
በመላኩ ገደፍ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!