ጉዳት የደረሰባቸው የሰሜን ሸዋና የደቡብ ወሎ አካባቢዎችን መልሶ በማቋቋም አበረታች ስራዎች እየተሰሩ መሆኑ ተጠቆመ
አዲስ አበባ፣ ጥር 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በአሸባሪው የህወሓት ቡድን ጉዳት የደረሰባቸው የሰሜን ሸዋና ደቡብ ወሎ አካባቢዎችን መልሶ በማቋቋም አበረታች ስራዎች እየተሰሩ ስለመሆኑ ጠቁሟል።
በአምባሳደር ዶክተር የሺመብራት መርሻ የተመራው የቋሚ ኮሚቴው ቡድን በአካባቢው የመስክ ምልከታ እያደረገ ይገኛል።
የቋሚ ኮሚቴው አባላት በሸዋሮቢት፣ አጣዬ፣ ከሚሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞች በአሸባሪው የህወሓት ቡድን የደረሰውን ጉዳት ተመልክተው በየከተሞቹ ካሉት አመራሮች ጋር ተወያይተዋል።
በሸዋሮቢት ጉዳት ለደረሰባቸው ነዋሪዎች ከመንግስታዊና መንግታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የምግብና መሰረታዊ ቁሳቁሶች ድጋፍ እየተደረገ ቢሆንም፥ ተጎጂዎቹን በዘላቂነት ለማቋቋም ግን የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ጥረት እንደሚጠይቅ የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ጌታሁን ስዩም ለቋሚ ኮሚቴው አባላት አስረድተዋል።
የአጣዬ ከተማ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የሚያስችል የአመራር ሪፎርም በመደረጉ ከአጎራባች ወረዳዎች ጋር ተደጋግፈው እየሰሩ ስለመሆኑ የከተማዋ ምክትል ከንቲባ አቶ ወንደሰን ተገኝ ገልፀዋል።
በከሚሴ አካባቢ ሰላም ወደ ቀድሞ እየተመለሰ መሆኑን ከቋሚ ኮሚቴው አባላት ጋር የተወያዩ የሀገር ሽማግሌዎች ገልጸው፥ በአሸባሪዎቹ የሸኔና የህወሓት ቡድኖች የወደሙት የከሚሴ ከተማ ጤና ተቋማት ለአጎራባች አካባቢዎች ጭምር አገልግሎት እየሰጡ የነበረ በመሆኑ ልዩ ትኩረት እንደሚያስፈልጋቸው የከተማዋ አመራሮች ጠይቀዋል።
የፌዴራልና የክልሉ መንግስት የኮምቦልቻ ከተማን መልሶ በማቋቋም ረገድ ርብርብ እያደረጉ ነው ያሉት የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር አህመድ የሱፍ ናቸው።
በየአካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎች እርስ በርስ በመረዳዳት የመልሶ ማቋቋም ስራውን ሊያፋጥኑ እንደሚገባ የቋሚ ኮሚቴው ቡድን መሪ ዶክተር የሺመብራት ለየአካባቢው አመራሮች በሰጡት ግብረ መልስ ጠቅሰዋል።
በየአካባቢው የተጀመረው የአመራር ሪፎርም በጥናት ላይ ተመስርቶ እንዲቀጥል የቋሚ ኮሚቴው አባላት አሳስበው፥ ጉዳት የደረሰባቸውን ለማገዝ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር እንደሚሰሩም መግለጻቸውን ከተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!