ኤፍ ኤች ኢትዮጵያ የተባለው ግብረ ሰናይ ድርጅት በአማራ ክልል የ6 ቢሊዮን ብር ፕሮጀክቶች ተፈራረመ
አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኤፍ ኤች ኢትዮጵያ የተባለው ግብረ ሰናይ ድርጅት በአሜሪካው ተራድኦ ድርጅት እገዛ በአማራ ክልል ለአምስት ዓመታት የሚቆይ የ6 ቢሊዮን ብር ፕሮጀክቶች ከፈፃሚ አካላት ጋር ተፈራረመ።
ድርጅቱ ባለፉት አምስት ዓመታት በነበረው ፕሮግራም በተለያዩ ዘርፎች የበጎ አድራጎት ተግባራትን ሲፈጽም መቆየቱን በግብረ ሰናይ ድርጅቱ የአንድ ፕሮግራም ምክትል ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ጌታሁን ሺበሺ ተናግረዋል።
አቶ ጌታሁን በሰጡት ማብራሪያ፥ ድርጅቱ የተለያዩ የጤናና የትምህርት ተቋማት ግንባታ ሲሠራ መቆየቱንና ሁሉን አቀፍ የምግብ ዋስትና ተግባራትን መፈጸሙንም ጠቅሰዋል።
ድርጅቱ የመንግሥት ፕሮግራሞችን ሲደግፍ መቆየቱንም አስረድተዋል።
የድርጅቱ በተጋላጭነትና የምግብ ዋስትና ክፍተት የሚሞላ ፕሮግራም ዋና አስተባባሪ ግርማ ዴሬሳ በበኩላቸው፥ በሽብር ቡድኑ የተጎዱ አካባቢዎች ስለተጠኑ ፕሮጀክቶቹ በኅብረተሰቡ ፍላጎት መሠረት ተግባራዊ ይደረጋሉ ብለዋል።
በምግብ ራሳቸውን ያልቻሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ራሳቸውን እንዲችሉና በሂደትም ከድህነት እንዲወጡ ለማድረግ ይሠራል ነው ያሉት።
ድርጅቱ በሴፍቲኔት ፕሮግራሙ መንግሥትን የመደገፍ ተግባራት እንደሚፈጽም አቶ ግርማ ገልጸዋል፡፡
የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ኀላፊ ዶ/ር ጥላሁን መሐሪ በክልሉ በርካታ ወረዳዎች በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን የተጎዱ ስለሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የድጋፍ ተደራሽነት ሊያሰፉ እንደሚገባ ጠይቀዋል።
ድርጅቱ በሚሠራበት አካባቢ ሁሉ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባም ኀላፊው አሳስበዋል፡፡
ኤፍ ኤች ኢትዮጵያ በአማራ ክልል በሴቶች፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በውኃ፣ በቴክኒክና ሙያ፣ በግብርና እና በሌሎችም ከመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ጋር በመተባበር እንደሚሰራ አሚኮ ዘግቧል፡፡