የኢትዮጵያ ትረስት ፈንድ በአማራና አፋር ክልሎች ትምህርት ቤቶችን ሊያስገነባ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ትረስት ፈንድ በአማራና አፋር ክልሎች በ3 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር አራት ትምህርት ቤቶችን ሊያስገነባ መሆኑ ተገለፀ፡፡
በጦርነት በተጎዱ አካባቢዎች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት በትምህርት ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ መካከል የአጋርነት ስምምነት ተደርጓል።
የትምህርት ሚኒስቴር በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ከኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማህበር ጋር በመሆን ወጥ የሆነ ዲዛይን ያዘጋጀ መሆኑን የገለጹት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፥ አሁን በአማራና አፋር ክልል የሚገነቡት ትምህርት ቤቶችም በዚሁ ዲዛይን የሚሰሩ እንደሆነ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ትምህርት አሁን በፈረሱት ትምህርት ቤቶች ብቻ አይደለም ጉዳት የደረሰበት፤ ከዚህ በፊትም በስርዓተ ትምህርቱ አማካኝነት ብዙ ተጎድቷል ያሉት ሚኒስትሩ አሁን የትምህርት ጥራቱን በሚያሻሽል መልኩ የፈረሱትን ትምህርት ቤቶች በተሻለ ሁኔታ እንገነባለን ብለዋል።
ትረስት ፈንዱ የሚያስገነባቸው ትምህርት ቤቶች 3 ሺህ 800 ተማሪዎችን የሚያገለግል እንደሆነ ገልጸዋል።
ግንባታውንም በኢትዮጵያ ኮሚቴ በማቋቋምና ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በየጊዜው መረጃ በመለዋወጥ እንደሚከታተሉት አስታውቀዋል።
በአማራ ክልል ሁለት በአፋር ክልል ሁለት ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት የታሰበ ሲሆን÷ ግንባታውንም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዟል።
የአማራና የአፋር ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊዎችም የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
በዘመን በየነ