Fana: At a Speed of Life!

ፋና የሀገርን ከፍታ በሚያረጋግጥ መልኩ ትውልዱ እውቀትን፣ ጥበብንና ስነ ምግባርን እንዲያዳብር የሚጫወተውን ሚና አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋገጠ

አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሀገርን ከፍታ በሚያረጋግጥ መልኩ ትውልዱ እውቀትን፣ ክህሎትን፣ ጥበብን እና ስነ ምግባርን እንዲያዳብር ፋና እየተጫወተ ያለውን ሚና አጠናክሮ እንደሚቀጥል የተቋሙ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው አረጋገጡ።
 
ለወራት ተቋርጦ የነበረው ፋና ላምሮት የባለተሰጥኦ ድምጻውያን ውድድር ዛሬ በ9ኛ ምእራፍ ተጀምሯል።
 
በማስጀመሪያ ስነ ስርዓት ላይ የተገኙት ዋና ስራ አስፈፃሚው፥ በተደቀነው የህልውና አደጋ ምክንያት የፋና ላምሮት ፕሮግራም ለተወሰነ ጊዜ ተቋርጦ እንደነበር አስታውሰዋል።
 
ይሁን እንጂ ጀግኖች ኢትዮጵያዊያን ባደረጉት ተጋድሎ ሀገርን ከመፍረስ በማዳን የኢትዮጵያን ክብር አስመልሰዋል ብለዋል አቶ አድማሱ።
 
በዚህ ሂደትም ጀግኖች ለሀገር ክብር ዋጋ ሲከፍሉ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በኢትዮጵያዊያን ዘንድ የአሸናፊነት ስነ ልቦና እንዲሰርፅ እና በመረጃ የበለፀገ ማህበረሰብን በመፍጠር ውስጥ የማይናቅ ሚና እየተጫወተ ያለ ሚዲያ እንደሆነ ተናግረዋል።
 
እንደ ፋና ላምሮት ያሉ የሚዲያ ይዘቶች ደግሞ የህብረተሰቡን ፍላጎትና ተሳትፎ በማሳደግ የባለቤትነት ስሜት እንዲኖር በማድረግ በኩል ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ ነው ዋና ስራ አስፈጻሚው የተናገሩት።
 
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በይዘቶቹ የትውልድ ቅብብሎሽ ስራን ይሰራል ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው አቶ አድማሱ፥ የሀገርን ከፍታ ለማረጋገጥ ትውልዱ ጥበብን፣ ስነምግባርን፣ እውቀትንና ክህሎትን እንዲያዳብር በማድረግ ሚናውን እየተወጣ መሆኑንም አመላክተዋል።
በተለይም ፋና ላምሮት ጥበበኞችን ከፍ በማድርግ፣ ውለታቸውን በማክበር እና በማስከበር ታሪክን ሰንቆ ለነገ በማቆየት እያከናወነ ያለውን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያረጋገጡት።
 
የፋና ላምሮት 9ኛ ምእራፍ ከጀመረ በኋላም እንደ ትናንቱ ሁሉ ትውልድ እንዲቀጥል፣ የጥበብ ውጤቶች በየአደባባዩ ክብር እና ዝና እንዲያገኙ በዛው ልክ ደግሞ በእውቀትና በስነ ምግባር እንዲመሩ ለማድረግ ፋና የተጣለበትን ሀላፊነት እንደሚወጣም አስታውቀዋል።
 
ፋና ላምሮት በዘጠነኛው ምእራፍ 12 ተወዳዳሪዎች የሚፎካከሩ ሲሆን፥ ለፍፃሚ የሚደርሱ አራት ተወዳዳደሪዎች የ500 ሺህ ብር ተሸላሚ ይሆናሉ።
 
በየምእራፎቹ አሸናፊ የሆኑ ተወዳዳሪዎች ደግሞ ወደ ታላቁ የአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድር በቀጥታ ይገባሉ።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.