ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከተማ አቀፍ የፅዳት ንቅናቄን አስጀመሩ
አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በቂርቆስ ክ/ከተማ በመገኘት ከተማ አቀፍ የፅዳት ንቅናቄውን አስጀመሩ፡፡
እንደሚታወቀው ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ 35ኛውን የአፍሪካ ጉባኤ መሰረት በማድረግ የፅዳት ዘመቻ በመላው ከተማይቱ እንደሚካሄድ ጥሪ ማስተላለፋቸው አይዘነጋም፡፡
ይህንን ጥሪ ተከትሎ ዛሬ በመላው ከተማይቱ የፅዳት ፕሮግራም እየተካሄደ ሲሆን ከንቲባ አዳነች አቤቤ በቂርቆስ ክ/ከተማ በመገኘት ከነዋሪዎች ጋር የፅዳት ፕሮግራሙን በይፋ አስጀምረዋል፡፡
በዚህ ፕሮግራም ላይ ንግግር ያደረጉት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እንደተናገሩት የአፍሪካ ጉባኤ ስናስተናግድ በዛ አስቸጋሪ ወቅት አዲስ አበባ ተከባለች ኑ ውጡ ሲባሉ ኢትዮጵያ ስትቸገር አብረናት እንቆማለን ፤ እናታችን ናት ፤ኢትዮጵያን ጥለን ወዴት እንሄዳለን በማለት ፤ ከጎነችን የቆሙት የአፍሪካ ወንድሞቻችን ያለንን አክብሮትና ፍቅር የምንገልፅበት ነው፡፡
በተለይም ይህ ጉባኤ ኢትዮጵያ ጉባኤውን ማዘጋጀት እንደምትችል የራሷን ሰላም በራሷ ማረጋገጥ እንደምትችል ያሳየና የውጪ ሃይሎን ጉዳይ ጣልቃ መግባት ይቅር በማለት በ NoMore ንቅናቄ ከጎናችን በመሆን አጋርነታቸውን ስላሳዩን ለአፍሪካውያን አድናቆታችን የምናሳይበት ነው ብለዋል፡፡
በአፍሪካ ወንድሞቻችን እንኮራለን! በአፍሪካዊነታችንም እንኮራለን ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ፤ ይህ ጉባኤ ለየት የሚያደርገው ዳግም ለአፍሪካ ነፃነት ፋና ወጊነታችንን ያሳየንበት ወቅት መሆኑ ነው፡፡
የፅዳት ንቅናቄው ሳምንቱን ሙሉ በተከታታይ በየእለቱ መካሄዱን እንደሚቀጥል ከንቲባዋ በዚሁ አጋጣሚ መናገራቸውን ከከንቲባ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡