አምባሳደር አለምፀሀይ መሰረት ከኡጋንዳ የምድር ጦር ዋና አዛዥ ሌ/ጄ ሙሆዚ ካኒሩጋባ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኡጋንዳ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር አለምፀሀይ መሰረት ከሀገሪቱ የምድር ጦር አዛዥ እና ከልዩ ኦፕሬሽን ፕሬዚዳንት አማካሪ ሌተናል ጄኔራል ሙሆዚ ካኒሩጋባ ጋር በሀገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነት እና በቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል፡፡
በውይይቱም ኢትዮጵያ እና ኡጋንዳ ታሪካዊና ዲፕሎማሲያዊ መልካም ግንኙነት እንዳላቸው በማንሳት በኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ እና መከላከያ ዘርፎች ያላቸውን ትብብር የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባ ተገልጿል።
ኢትዮጵያ ላለፉት ሶስት አመታት ያካሄደችውን ሁለንተናዊ ለውጦች፣ በሀገሪቱ ስላሉ ወቅታዊ ሁኔታዎች እና በህወሓት አሸባሪ ቡድን ሀገራችን ላይ የተከፈተውን ጦርነት እና ውድመትን በተመለከተ አምባሳደር አለምጸሀይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ሌተናል ጄኔራል ሙሆዚ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ተምሳሌት የሆነች፣ በቀጠናው ታላቅ ሚና ያላት ታላቅ አገር እንደሆነች፣ በተለይም ደግሞ በርካታ ኡጋንዳውያን ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይ ባህል የሚጋሩና ትስስር ያላቸው መሆኑን በማንሳት በዚህም ኢትዮጵያ ሰላም ሆና ማየት እንደሚሹ ገልፀዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት ሀገሪቱ ባካሄደችው ለውጥ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ያላቸውን አድናቆት በመግለጽ አሁንም ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ጊዜያዊ ችግር ለመፍታት ብቁና ቁርጠኛ አመራር ያላት አገር መሆኗን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከኡጋንዳ መንግስት ሆነ ከፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ለምትፈልገው ማንኛውም ድጋፍ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን ሌተናል ጄኔራሉ ማስረዳታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!