Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል የተፈጠረውን የነዳጅ እጥረት ለመፍታት በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የተፈጠረውን የነዳጅ እጥረት ለመፍታት በትኩረት እና በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በአማራ ክልል የነዳጅ እጥረትን በዘላቂነት መፍታት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እና ከከተማ አስተዳድር ኃላፊዎች ጋር በባህር ዳር ከተማ ተወያየ፡፡

የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ታደሰ ሃይለማሪያም÷ በክልሉ የነዳጅ እጥረት የሚከሰተው የነዳጅ አቅራቢ ኩባንያው ለክልሉ ማድረስ ያለበት ነዳጅ ለማደያዎች በትክክል መድረስ አለመድረሱን ክትትልና ቁጥጥር ባለመደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ነዳጅ በኮንትሮባንድ ወደ ጎረቤት ሀገራት በማውጣት እየተሸጠ መሆኑ ለእጥርቱ አንዱ ምክንያት መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

በክልሉ የነዳጅ እጥረትን በዘላቂነት ለመፍታት የማደያዎችንና የዴፓ ቁጥር መጨመር፣ በህገ ወጥ ነጋዴዎች እንቅስቃሴ ላይ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግና የመረጃ ቅብብሎሹን በማዘመን ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩል በኮንትሮባንድ ከሀገር የሚወጣውን ነዳጅ ለማስቀረት የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡

በርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አማካሪ ወይዘሮ አይናለም ንጉሴ በበኩላቸው÷ በኢትዮጵያ የነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ድልድሉ ፍትሃዊ እንዲሆን ማድረግ እና በባህር ዳር ከተማ ለመገንባት የታቀደው የዴፖ ግንባታ መፋጠን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ህገ ወጥ ነጋዴዎችን በመቆጣጠር በክልሉ የተፈጠረውን የነዳጅ እጥረት ለመቅረፍ በኩል ድርጅቱ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ መጠቆማቸውን ከአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የክልሉ ንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ ቀለምወርቅ ምህረቴ ÷ በክልሉ የተፈጠረውን የነዳጅ እጥረት ለመፍታት መንግስት ከሌሎች መሰረታዊ ምርቶች ጋር አቀናጅቶ ከፍተኛ ድጎማ እያደረገ ቢሆንም አንዳንድ ባለሀቶች በህገ ወጥ መንገድ ለመበልጸግ ችግሩ እንዲባባስ እያደረጉ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የትራንስፖርቱን ዘርፍ በተገቢው መንገድ በማንቀሳቀስ ኢኮኖሚውን ማስቀጠል ስለሚገባ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩሉን እንዲወጣ፤ በተለይም ባለሃብቱ በማደያ ግንባታ እንዲሳተፍ ጠይቀዋል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.