የሆሞሻ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ምዕራፍ አስፋልት መንገድ ግንባታ ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ጥር 23 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሆሞሻ ህዳሴ ግድብ 100 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ መጀመሩን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣ አስታወቀ፡፡
በባለስልጣኑ የምዕራብ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት አስተዳደር ቡድን አንድ መሪ አቶ ካሊድ ዓሊ እንደገለጹት÷ የአስፋልት መንገዱ ግንባታ በሁለት ምዕራፎች ተከፍሎ የሚከናወን ነው።
መንገዱ የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ ከሆሞሻ ጀምሮ 70 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን መሆኑን ጠቁመው፥ በአሁኑ ወቅት የቅየሳ ስራው 80 በመቶ መጠናቀቁን ገልጸዋል።
ለመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታው የሚያገለግሉ የአሸዋና ድንጋ መረጣና አቅርቦት ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
የመጀመሪያው ምዕራፍ ስራው የ70 ኪሎ ሜትር አስፋልት መንገድ ግንባታ በሶስት ዓመት ከስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ እንደሚከናወን ነው የገለጹት።
መንገዱ በሚያቋርጣቸው የሆሞሻ፣ መንጌና ሸርቆሌ ከተሞች የ30 ሜትር፥ ከከተሞች ውጪ ደግሞ 10 ሜትር ስፋት እንደሚኖረውም አስረድተዋል።
ለመንገድ ግንባታው የሚያስፈልገው ከ2 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በላይ በጀት በፌዴራል መንግሥት እንደሚሸፈን የቡድን መሪው ጠቅሰዋል።
በሁለተኛው ምዕራፍ የሚገነባው እስከ ህዳሴ ግድብ ድረስ ያለውን ቀሪው 30 ኪሎ ሜትር መንገድ ግንባታ በተያዘው በጀት ዓመት ጫረታው እንደሚወጣ ነው አቶ ካሊድ ያሳወቁት።
የአስፋልት መንገዱ የህዳሴው ግድብ ሲጠናቀቅ በአካባቢው የሚፈጠሩትን የኢንቨስትመንት አማራጮች በማስፋት ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
የክልሉ መንገድና ትራንስፖር ቢሮ የመንገድ ጥናት፣ ዲዛይንና ቁጥጥር ኮንትራት አስተዳደር ዳይሬክተር ኢንጅነር በፍቃዱ ዮሴፍ እንዳሉት ÷ ከግለሰቦች ይዞታ ጋር ተያይዞ አለመግባባቶ እንዳይከሰቱ ከመንገድ ቅየሳ ጀምሮ በመግባባት መሰራቱን አስረድተዋል።
ይህም የመንገድ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ራሱን የቻለ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የመንገዱ ግንባታው የጥራት ደረጃውን ጠብቆ እንዲካሄድ በቅንጅት እየተከናወኑ ያሉ ተግበራትም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው ዳይሬክተሩ የተናገሩት፡፡