የባህል፣ ዕደ ጥበብና ኪነ ጥበብ ዘርፍ ለልማት ያለውን ሚና ለማሳደግ እየተሰራ ነው- አቶ ቀጄላ መርዳሳ
አዲስ አበባ፣ ጥር 23 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የባህል፣ ዕደ ጥበብና ኪነ ጥበብ ዘርፍ በሀገሪቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ያለውን ሚና ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጄላ መርዳሳ ገለጹ።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ግምገማውን በአዳማ ከዘርፉ መሥሪያ ቤቶች ጋር እየገመገመ መሆኑ ተገልጿል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጄላ መርዳሳ ባለፉት ዓመታት የባህል፣ የዕደ ጥበብና ኪነ ጥበብ ዘርፍ በሀገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት ውስጥ የሚጫወተውን ሚና ከፍ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የባህል እሴቶች፣ ዕደ ጥበብና ኪነ ጥበብ በሀገር ገፅታ ግንባታ ጉልህ ሚና ሊኖራቸው ይገባል ያሉት አቶ ቀጄላ÷ይህን የሚሆነው ተገቢውን ትኩረት አግኝተው መልማትና መዘመን ሲችሉ መሆኑን አስረድተዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት የባህል እሴቶች በህዝቦች መቻቻልና አብሮነት በተለይ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር መሰራቱን አስታውቀዋል።
በተመሳሳይ ብሔራዊ የስፖርት መሠረተ ልማት ግንባታን ለማፋጠን ጥረት መደረጉንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በሚኒስቴሩ የባህልና ቋንቋ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ወርቅነሽ ብሩ በበኩላቸው ÷ ኢትዮጵያ ከገጠሟት ችግሮች ለመውጣት የባህል እሴቶች ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።
በዚህም በሕዝቦች መካከል ጠንካራ የባህል ትስስርና ግንኙነት በመፍጠር ትኩረት መሰጠቱን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ÷ ባህላዊ እሴቶች የችግሮች መፍቻ እንዲሆኑ የተቀናጀ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
በቋንቋ ልማት በኩል ስድስት ጥናቶች መካሄዳቸውን ጠቁመው÷ በዚህም የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቋንቋዎች ያሉበትን ሁኔታ በመለየት በሰነድ አደራጅቶ ለመያዝ እየተሰራ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ከአማርኛ በተጨማሪ አፋን ኦሮሞ፣ ሶማሊኛ፣ አፋርኛና ትግርኛን የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ ለማድረግ ረቅቅ የፖሊሲ ሰነድ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል።