አዲሱ ትውልድ በንባብ የዳበረ ዕውቀት እንዲኖረው መሥራት ይገባል-ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ
አዲስ አበባ፣ ጥር 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አዲሱን ትውልድ በንባብ የዳበረ ዕውቀት እንዲኖረው ደረጃቸውን የጠበቁ ቤተ መጻህፍት ማስፋፋት እንደሚገባ አምባሳደር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ አመለከቱ።
የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከ106 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ያስገነባው ዘመናዊ ሁለገብ ቤተ መጻህፍት ዛሬ የተመረቀ ሲሆን÷ በየኒቨርሲቲው ሥር ለተቋቋመው ለኢትዮጵያ ቴክስታይል፣ ፋሽንና ቴክኖሎጂ አገልግሎት እንደሚሰጥ ተገልጿል።
የዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አምባሳደር ዶክተር ኢንጂር ስለሺ በቀለ በምረቃው ላይ እንዳሉት ቤተ መፅሃፍቱ ትውልዱን ከማህበራዊ ሚዲያ ጥገኝነት ደረጃ በደረጃ በማላቀቅ በንባብ የዳበረ እውቀትና ክህሎት ለመጨበጥ እንደሚረዳው አመልክተዋል።
የዩኒቨርሲቲው ሌሎች የትምህርት ክፍሎችም ሳይንስን ለማስፋፋት መሰል ቤተ መጻህፍትን እንዲከፍቱም አሳስበዋል።
የተቋሙ ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶክተር ታምራት ተስፋዬ በበኩላቸው፥ ቤተ-መጻህፍቱ የህፃናት፣ የሴቶች፣ የቅድመና ድህረ ምረቃ ተማሪዎች እንዲሁም ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ክፍሎች እንዳሉት አመልክተዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ “ቤተ-መጻህፍቱ በፋሽንና ዲዛይን ዘርፍ ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ሃይል በማፍራት በተለይ የባህር ዳርን የቱሪዝም ዘርፍ የሚያሳልጡ ባለሙያዎችን ለማፍራት እገዛ ያደርጋል” ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ቤተ መፅሃፍቱ የማንበቢያ ሰገነት፣ የማንበቢያ አረንጓዴ ስፍራና ካፍቴሪያ፣ ሙዚዬምና ዲጂታል- ቤተ መጻህፍትን አካቶ የያዘ መሆኑ ታውቋል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!