የምዕራብ ዕዝ የሽብር ቡድኑን መዋቅር በማፈራረስና የህግ ማስከበር ዘመቻው በአጭር ጊዜ እንዲቋጭ የአንበሳውን ድርሻ ተወጥቷል- ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ
አዲስ አበባ፣ ጥር 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የምዕራብ ዕዝ የሽብር ቡድኑን መዋቅር በማፈራረስና የህግ ማስከበር ዘመቻው በአጭር ጊዜ እንዲቋጭ በማድረግ የአንበሳውን ድርሻ መወጣቱን ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለፁ።
ዕዙ በ3 ደረጃዎች የሜዳልያ ሽልማት የሰጠ ሲሆን ፥ በእውቅናው አመራሮች ፣ አባላትና ክፍሎች ተሸላሚ ሆነዋል።
በሥነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፥ ለጀግኖች ሜዳልያ ከሸለሙ በኋላ ንግግር አድርገዋል።
በንግግራቸውም፥ የምዕራብ ዕዝ በሰራዊታችን ላይ የክህደት ተግባር የፈፀመውን የአሸባሪውን ቡድን ቁንጮ ፖለቲካዊና ወታደራዊ አመራሮች በመደምሰስና በቁጥጥር ስር በማዋል የህግ ማስከበር ዘመቻው በአጭር ጊዜ እንዲቋጭ የአንበሳውን ድርሻ የተወጣ ዕዝ ነው ብለዋል።
ተሸላሚዎቹ አገርን ከመፍረስ ለማዳን ባደረጉት ተጋድሎ ሽልማቱ እንደተሰጣቸው የገለፁት ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ፥ ሽልማቱ ለተመረጡ አባላት ቢሰጥም ስራው ግን የሁሉም አመራርና አባል የጋራ ውጤት እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል ነው ያሉት።
ለቀጣይ ግዳጅም ራስን ማዘጋጀት ይጠይቃል ብለዋል።
የምዕራብ ዕዝ አዛዥ ሌ/ጄ መሰለ መሰረት በበኩላቸው ፥ የምዕራብ ዕዝ ላለፉት 15 ወራት የአሸባሪውን ቡድን አከርካሪ ለመስበር በሰው ኃይል፣ በቁሳቁስና በሞራል ደረጃ እንዲዳከም ያደረገና የሽብር ቡድኑ ሰሜን ዕዝ ላይ ያደረገውን አፈና በመቀልበስ በእግር ረጅም ርቀት በመጓዝ የተቋሙን ፍላጎት ያሳካ ዕዝ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህ ጦርነት በርካታ ጀግኖችን ማፍራት መቻሉን ፣ ለቀጣይ ለግዳጅም በቂ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል።
ተሸላሚዎቹም ፣ ሽልማቱ ለቀጣይ ግዳጅ ተጨማሪ ኃላፊነትን የሚያጎናፅፍ በመሆኑ ለሀገር ሉዓላዊነት መከበር አስፈላጊውን ሁሉ መስዋዕትነት እንደሚከፍሉ መናገራቸውን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!