በደሴ ከተማ የተለያዩ ሀሰተኛ የብር ኖቶች እና ሕገ ወጥ ጥይቶች ተያዙ
አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በደሴ ከተማ በአራዳ ገበያ ማዕከል የተለያዩ ሀሰተኛ የብር ኖቶችን ጨምሮ የሽጉጥና የብሬን ጥይቶች እና 8 ካዝናዎች መያዛቸውን የደሴ ከተማ አንደኛ ዋና ፖሊስ ጣቢያ አስታወቀ፡፡
የጣቢያው የማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ኃላፊ ረዳት ኢንስፔክተር መሀመድ አሊ እንደገለጹት÷ በአራዳ የገበያ ማዕከል አካባቢ ተጠርጣሪው ግለሰብ በሀሰተኛ የብር ኖት ልብስ ሊገዛ ሲል በህብረተሰቡ ትብብር ባለ ሁለት መቶ ብር 9 ሺህ 400 ሀሰተኛ የብር ኖቶች ይዞ ተገኝቷል፡፡
ተጠርጣሪው ተጨማሪ ሀሰተኛ ብር ሊኖረው ይችላል በሚል ጥርጣሬ በተደረገ ፍተሻ÷ 200 የሽጉጥ ጥይቶች፣ 52 የብሬን ጥይቶች እና 8 ካዝናዎች ተገኝቶበታል ብለዋል፡፡
ጉዳዩ በህግ እየታየ መሆኑን የገለጹት ኢንፔክተር መሀመድ÷ የጸጥታ ኃይሉም በልዩ ትኩረት ተመሳሳይ ወንጀሎችን ለመከላከል እየሰራ መሆኑ ተናግረዋል፡፡
አሸባሪው የህወሓት ቡድን በከተማዋ በቆየበት ወቅት የተለያዩ የሀሰተኛ የብር ኖቶችን ጥሎ በመሄዱ ህብረተሰቡ እና የንግዱ ማህበረሰብ እራሱን እንዲጠብቅ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ከጣቢያው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!