በአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከልና ተጽዕኖውን ለመቋቋም የሚያስችል ስትራቴጂ ተዘጋጀ
አዲስ አበባ፣ጥር 29፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፍሪካ ለቀጣይ ሁለት ዓመታት ገቢራዊ የሚሆን የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከከልና መቋቋም የሚያስችል ስትራቴጂ መዘጋጀቱን አፍሪካ ኅብረት የዘርፉ አስተባበሪ የሆኑት የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛ ገለጹ።
በአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን የአፍሪካ አገራት መሪዎች በአየር ንብረት ለውጥ ያላቸው አቋምን ለማንጸባረቅና በዓለም መድረክ ላይ በአንድ ድምጽ እንዲወከሉ ለማስቻል የተቋቋመው ኮሚቴ (ኮሶክ) ስብሰባ ዛሬ ተካሂዷል።
ላለፉት ዓመታት ኮሚቴውን በማስተባበር ኃላፊነት የተሰጣት ደቡብ አፍሪካ በቆይታዋ በአየር ንብረት ጉዳይ ላይ አፍሪካን አቋም ለማንጸባረቅ ስትሰራ መቆየቷን ነው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛ የጠቆሙት።
ያም ሆኖ በአህጉሪቱ በተደጋጋሚ የሚከሰቱ እንደ ድርቅ፣ ጎርፍና ዝናብ ያዘለ ከባድ ንፋስ (ሳይክሎን) የአየር ንብረት ለውጥ አፍሪካን በእጅጉ እየጎዳት መሆኑን እንደሚያመላክት አስረድተዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ የአፍሪካ አገራት ከጥቅል አገራዊ ምርት ከሚያገኙት ገቢ በየዓመቱ ከ3 እስከ 5 በመቶ እንደሚያሳጣ ጠቁመው፤ ጉዳዩ ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል።
የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተከትሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀዛቀዘውን የባለብዙ ወገን ትብብሮችን አጠናክሮ በመቀጠል የዓለም ችግር ለሆነው የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄ ማበጀት እንደሚገባ ገልጸዋል።
በዚህም ለቀጣይ ሁለት ዓመታት ገቢራዊ የሚሆን አህጉራዊ የአየር ንብረት ለውጥ የመከላከያና መቋቋሚያ ስትራቴጂ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።
ስትራቴጂው የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚያስችሉ የተለያዩ የትግበራ እቅዶችን የያዘ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም የሚተገበሩ አህጉራዊ ኢኒሼቲቮችን ለማስቀጠል እንደሚያስችል ተናግረዋል።
በካርቦን ልቀት ቅነሳ፣ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም እና የታዳሽ ኃይል ተጠቃሚነትን ማጎልበት በሚለው ስትራቴጂ ላይ ትኩረት እንደሚያደርግም ገልጸዋል።
አፍሪካ በቀጣይ በግብጽ በሚካሄደው የዓለም የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ አንድ የጋራ ድምጽ ለማሰማት የሚያስችላትን የጋራ አቋም እንድታንጸባርቅ በጉዳዩ ላይ የራሷን አጀንዳ ከወዲሁ ቀርጻ መንቀሳቀስ እንደሚገባት ተናግረዋል።
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽነር ሙሳ ፋቂ ማኅማት፤ የአየር ንብረት ለውጥ በአፍሪካ ከባድ አደጋ ያለው መሆኑን በመረዳት የችግሩን አስከፊነት በማወቅ ሁሉም በጋራ ሊረባረብ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።
ደቡብ አፍሪካም ኮሚቴውን በማስተባበር ባለፉት ሁለት ዓመታት የአፍሪካ ድምጽ እንዲሰማ ላደረገችው ከፍተኛ አስተዋጽዖ ምስጋና አቅርበው፤ በቀጣይ በሚካሄደው የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ አፍሪካ ድምጿ እንዲሰማ ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የቀጣይ የኮሶክ አስተባባሪነት የተመረጠችው ሴኔጋል በተደራራቢ ኃላፊነትን ለመቀነስ ኅብረቱ ባደረገው ውሳኔ በኬንያ የተተካች ሲሆን፤ የኬንያው ፕሬዝዳንትም ውሳኔውን በይሁንታ ተቀብለውታል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።