Fana: At a Speed of Life!

ናርዶስ በቀለ የአፍሪካ ኅብረት የልማት ኤጀንሲ የመጀመሪያዋ ሴት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆነው ተሾሙ

አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ኅብረት ናርዶስ በቀለን የሕብረቱ የልማት ኤጀንሲ (ኔፓድ) የመጀመሪያዋ ሴት ስራ አስፈጻሚ አድርጎ ሾመ።
35ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በትናንት ውሎው ኢትዮጵያዊቷን ናርዶስ በቀለ የአፍሪካ ኅብረት የልማት ኤጀንሲ ዋና ስራ አስፈጻሚ አድርጎ መርጧል።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያዋ ናርዶስ በቀለ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተለያዩ ድርጅቶችና በተለያዩ አገራት በተሰጣቸው ተልዕኮዎች በኃላፊነት አገልግለዋል።
በአሁኑ ሰአት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የደቡብ አፍሪካ የዲፕሎማሲ ልዑክ ተወካይና በደቡብ አፍሪካ የተመድ የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) አስተባባሪ ናቸው።
ለ40 ዓመት ገደማ በአፍሪካ የልማትና የእድገት ስራዎች ላይ በሙያቸው አስተዋጽኦ እንዳደረጉም ተገልጿል።
ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ናርዶስ በቀለ የአፍሪካ ኅብረት የልማት ኤጀንሲ (ኔፓድ) ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆነው መሾማቸውን አስመልክቶ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን÷ ”በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያካበቱት ከፍተኛ ልምድ ለኔፓድ ትልቅ አቅም ይፈጥራል፤ ሴቶች ይችላሉ” ብለዋል።
ናርዶስ በቀለ ከወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት የልማት ኤጀንሲ ዋና ስራ አስፈጻሚ ኒጀራዊው ፖለቲከኛ ዶክተር ኢብራሂም አሳኔ ማያኪ ይረካባሉ ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡
አዲስ አጋርነት ለአፍሪካ ልማት (ኔፓድ) እ.አ.አ በ2001 የተቋቋመ ሲሆን÷ የአፍሪካ ኅብረት እ.አ.አ በ2018 በሞሪታኒያ ናውክቾት ባደረገው 31ኛው የመሪዎች ጉባኤው ላይ ኔፓድ የኅብረቱ የልማት ኤጀንሲ እንዲሆን መወሰኑ ይታወሳል፡፡
ዋና መቀመጫውን በደቡብ አፍሪካ ያደረገው ኔፓድ በአፍሪካ አገራት መካከል ያለው የኢኮኖሚ ትብብርና ትስስር ማጠናከር ላይ ትኩረቱን አድርጎ ይሰራል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.