Fana: At a Speed of Life!

ለሸኔ የሽብር ቡድን ሊላኩ የነበሩ ህገወጥ የጦር መሣሪያዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) መነሻውን በአዲሰ አበባ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ሰንዳፋ ከተማ ያደረገ አንድ የጦር መሣሪያ አዘዋዋሪ ግለሰብ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3 ኦ ሮ 34043 በሆነ ዶልፊን ተሽከርካሪ ውስጥ ሻግ (መሸሸጊያ) በመሰራት 4 ሺ 994 የክላሽ ጥይት ለአሸባሪው የሸኔ ቡድን በድብቅ ለማድረስ ሲንቀሳቀስ በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡
 
ጥይቶቹ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ለሚንቀሳቀሱ የሸኔ የሽብር ቡድን አባላት እንዲደርሱ የታቀዱ ነበሩ፡፡
 
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የተገኘውን መረጃ መነሻ በማድረግ ከኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በጋራ ባከናወኑት ክትትል አዲስ አበባ ከተማ አራዳ ክፍለ ከተማ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አካባቢ ሲደርስ ከአዲሰ አበባ ፖሊስ ጋር በመተባበር ተጠርጣሪው ከእነ ጦር መሣሪያው በቁጥጥር ስር እንዲውል ተደርጓል።
 
በተመሳሳይ ከኬንያ ለሸኔ የሽብር ቡድን የተላኩ 2 አር ጂ ዲ (RGD) ቦምቦች እና 2 ሳተላይት ስልኮች ከእነ ሲም ካርዳቸው በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ በድርጊቱ የተጠረጠሩት ሁለት ሰዎች 4 ሺ 990 የኢትዮጵያ ብር እና የተለያዩ የባንክ ደብተሮች በእጃቸው ተገኝቷል፡፡
 
ግለሰቦቹ መሣሪያዎቹንና ሌሎችንም ህገወጥ ቁሶች ከቢሾፍቱ አካባቢ ተቀብለው የሰሌዳ ቁጥሩ 2A 58721 በሆነ ፒካፕ ተሽከርካሪ በማጓጓዝ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ለሚገኙት የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች ለማቀበል በመንቀሳቀስ ላይ ነበሩ፡፡
 
በህገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውሩ በተሰማሩት ተጠርጣሪዎች ላይ ይደረግ በነበረው ክትትል ቡራዩ አካባቢ ሲደርሱ ከኦሮሚያ ፖሊስ ጋር በመተባበር በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን የኦሮሚያ ፖሊስን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል፡፡

 

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.