ጥቁር አንበሳ ዮርዳኖስ ሆስፒታል አካባቢ በደረሰ የእሳት ቃጠሎ 7 ቤቶች ወደሙ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 18፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ትናንት ምሽት ጥቁር አንበሳ ዮርዳኖስ ሆስፒታል አካባቢ በደረሰ የእሳት ቃጠሎ 7 ቤቶች ሙሉ በሙሉ መውደማቸው ተገለጸ።
ቃጠሎው ከምሽቱ 1 ሰዓት ከ30 አካባቢ የደረሰ ሲሆን፥ የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽን ባለሙያዎች ደርሰው ከአካባቢው ማህበረሰብና ከጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር መቆጣጠራቸው ነው የተነገረው።
በኮሚሽኑ የአራዳ ቅርንጫፍ ቡድን መሪ አቶ በዙ ገመቹ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ እሳቱ ሰባት መጠጥ ቤቶችና የመኖሪያ ቤቶችን ሙሉ በሙሉ አውድሟል።
እሳቱን ለመቆጣጠር ከአምስት ቅርንጫፎች 24 ባለሙያዎች መሳተፋቸውንና 30 ሺህ ሊትር ውሃ ጥቅም ላይ መዋሉን አስረድተዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች የኤሌክትሪክ መስመር ቶሎ አለመቋረጡ ለእሳት አደጋው መባባስ ምክንያት እንደነበር አንስተዋል።
የአደጋው መንስኤና የደረሰው ዝርዝር የጉዳት መጠን ላይ ምርመራ እየተደረገ መሆኑንም አቶ በዙ ተናግረዋል፡፡
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision