አሜሪካ የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ የሰብዓዊ ድጋፍን መሰረት በማድረግ ግጭት ለማቆም መወሰኑን አጠብቃ እንደምትደግፍ ገለፀች
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዩናይትድ ስቴትስ የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል ለሚገኙ የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦቱ የተሳለጠ እንዲሆን ግጭት ማቆሙን በአወንታ እንደምትቀበል እና አጥብቃም እንደምትደግፍ አስታወቀች።
መንግስት በትግራይ ክልል ለሚገኙ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ ሲባል ግጭት ለማቆም መወሰኑን ትናንት መግለፁ ይታወቃል።
ይህን መግለጫ ተከትሎ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ትናንት ማምሻውን ባወጡት መግለጫ፥ ከትናንት ጀምሮ ተግባራዊ የሆነው ይህ የመንግስት ውሳኔን ተከትሎ የተሳለጠ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እንደሚኖር ዕምነታቸውን ገልፀዋል።
የመንግስት ውሳኔ ለትግራይ ክልል ብሎም ለሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ወሳኝ እርምጃ እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
ለመላው ኢትዮጵያውያን ደህንነትና ብልፅግና ለማረጋገጥ የሚያስችል የፖለቲካ መፍትሄ ለመስጠትም መሰረት የሚሆን ነው ብለዋል።
ሁሉም ወገኖች ይህንን ውሳኔ ዘላቂ የተኩስ አቁም ለማምጣት የሚያስችል ድርድርን ለማድረግ እንዲጠቀሙበት ዩናይትድ ስቴትስ ጥሪ ታቀርባለች ብለዋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ።
የኢትዮጵያ ህዝብ በቀጣይ ሰላማዊ ጊዜን እንዲያሳልፍ አሜሪካ የቻለችውን ድጋፍ ሁሉ ማድረጓን እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል።