Fana: At a Speed of Life!

አቶ ደመቀ መኮንን በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ለተጎዱ ወገኖች የሚደረገው ሰብዓዊ ድጋፍ በላቀ ደረጃ መጠናከር እንደሚገባው አሳሰቡ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ለተጎዱ ወገኖች በፌዴራል አስፈፃሚ አካላት የተጀመረው የሰብዓዊ ድጋፍ አገልግሎት አሰጣጥ የችግሩን ውስብስብነት ሊመጥን የሚችል የላቀ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አሳሰቡ።

የብሔራዊ አደጋ መከላከል ኮሚቴ በተፈጥሮ እና በሰው ሰራሽ አደጋዎች ለተጎዱ ወገኖች በሚደረገው የሰብዓዊ ድጋፍ አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት አጠቃላይ እንቅስቃሴውን ገምግሟል።

የብሔራዊ አደጋ መከላከል ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደመቀ መኮንን በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት፥ በአሁን ጊዜ መንግስት በጦርነት እና በድርቅ በተጎዱ አካቢዎች የሚኖሩ ወገኖችን የሰብዓዊ ድጋፍ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የሚያደርገው ሁሉ-አቀፍ እንቅስቃሴ የሚያበረታታ ነው።

እንደ አቶ ደመቀ ገለፃ፥ ችግሩ በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች የተጀመረው እንቅስቃሴ አበረታች ቢመሆኑን ገልጸው፥ ሆኖም ከችግሩ ውስብስብነት አኳያ የሚመጥን ፈጣን ምላሽ እና ቅንጅታዊ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ከጠላት ቁጥጥር ነፃ የወጡ አንዳንድ ኪስ ቦታዎችን ለሰብዓዊ ድጋፍ አገልግሎት በፍጥነት ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ስልት ነድፎ መንቀሳቀስ እንደሚጠይቅም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

የፌዴራል አስፈፃሚ አካላት እንደ ሀገር ለገጠመን ሰፊ እና ውስብስብ ፈተና በአጭር ጊዜ መፍትሄ ለማበጀት ቀዳሚ ትኩረት እና ክብደት ሰጥቶ በጋራ መረባረብ እንደሚገባቸውም አቶ ደመቀ አስገንዝበዋል።

በሀገሪቱ የተፈጥሮ እና የሰው ሰራሽ አደጋዎች ተደራርበው መከሰታቸው እርምጃችንን ፈታኝ አድርጎታል ያሉት አቶ ደመቀ፥ “በተግባር ልንሻገር የሚያስችል የተናበበ ዕቅድ፣ ግልፅ አሰራር እና ውጤታማ የሀብት አጠቃቀም ስልት ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል “ ማለታቸውን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በሌላ በኩል ከሳዑዲ ተመላሽ ወገኖችን ተቀብሎ በማስተናገድ ሂደት የሚገጥሙ ችግሮችን በፍጥነት እየፈቱ በአግባቡ ከቤተሰቦቻቸው የሚቀላቀሉበት መንገድ የጋራ አፅንኦት እና ምላሽ እንዲሰጠው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጥሪ አቅርበዋል።

 

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.