መንግስት ለኢኮኖሚው የሚያደርገው ድጎማ የሚመራበት ስርዓትን እያበጀ መሆኑን አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት ለኢኮኖሚው የሚያደርገው ድጎማ የሚመራበትን ስርዓት እያበጀ መሆኑን አስታወቀ።
ላለፉት በርካታ ዓመታት የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በመንግስት ድጎማ ላይ የተንጠለጠለ ስለመሆኑ ይነገራል።
መንግስት ከነዳጅ አንስቶ መሰረታዊ ሸቀጦችንም ሆነ ኢኮኖሚውን በብዛት እየደጎመም ቆይቷል።
ኢኮኖሚውን መደጎም በራሱ ችግር ባይሆንም መንግስት የትኩረት አቅጣጫው ሲቀየርና የበጀት እጥረት ሲገጥመው በድጎማ የቆመው ኢኮኖሚ ቀውስ እየተስተዋለበት ይገኛል።
ድጎማ በራሱ መደጎም የሚገባውን የህብረተሰብ ክፍል ከማገዝ አንጻር ትክክለኛ አማራጭ ተደርጎ እንደማይወሰድም የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ይናገራሉ።
መንግስት የድጎማ ስርዓቱን ማስተካከል ካልቻለ በትክክል መጠቀም የሚገባቸው አካላት ሳይጠቆሙ እንደሚቀሩም ነው ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ የተናገሩት።
የሚደረጉት ድጎማዎች ኑሮን ለማረጋጋት ታስቦ ቢሆንም አሁንም ግን በጥናት ላይ የተመሰረተ ባለመሆኑ የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት አልቻለም ነው የሚሉት።
ለአብነት ያህል መንግስት ነዳጅ ላይ ከፍተኛ ገንዘብ ቢደጉምም በዓለም አቀፍ ገበያ የሚሸጥበትና በሀገር ውስጥ ነዳጅ እየተከፋፈለበት ካለው ዋጋ አንጻር መንግስት ላይ የ120 ቢሊየን ብር ጉድለት እንዲገጥመው ምክንያት ሆኗል።
የመሰረታዊ ፍጆታ እቃዎች በድጎማ እንዲገቡ በማድረግ ሂደት ውስጥም ቢሆን መንግስት አላስፈላጊ ኪሳራ ውስጥ እንዲወድቅ አድርጎታል።
ለህዝቡ ሲል የሚያደርገው ድጎማ እንደኪሳራ የሚቆጠር ባይሆንም ድንገት የሚፈጠሩ ቀውሶች ግን ኢኮኖሚው ዘላቂ ዕድገት እንዳይኖረው ማስገደዳቸው አይቀሬ ነው።
ይህን ችግር ለመቅረፍ እና ድጎማው በትክክል ለታለመላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር እንዲደርስ ምን አይነት መንገድ መከተል ይገባል በሚለው ላይ መንግስት ጥናት እያደረገ እና አሰራሮችን እየለየ ስለመሆኑም ነው ዶክተር ፍጹም የተናገሩት።
በአንድ ጊዜ ከተለመደው የድጎማ ስርዓት ውልቅ ብሎ መውጣት እንደሚታሰበው ቀላል አይሆንም የሚሉት ዶክተር ፍጹም፥ በትክክል በድጎማ ሊጠቀሙ የሚገባቸው ዜጎች የባሰ ሊጎዱም የሚችሉ በመሆኑ ያንን ከግምት ባስገባ መልኩ ስርዓቱን ማጤን እንደሚያስፈልግ መንግስትም ያምናል ብለዋል።
መንግስት ኢኮኖሚውን በድጎማ ማስቀጠል አይኖርበትም ከተባለ ዋናው መፍትሄው ኢኮኖሚውን እንዴት ለገበያው ይተው የሚለው ነው።
በመሆኑም በድጎማ ምክንያት የሚመጣውን የኢኮኖሚ መዛባት ለማስተካከል ኢኮኖሚው በገበያ እንዲመራ ማድረግ መፍትሄ እንደሆነ የሚያነሱት ሚኒስትሯ፥ ነገር ግን መንግስት እዚያ ለመድረስ አስፈላጊ መደላድሎችን መፍጠር ላይ እንደሚያተኩር ጠቁመዋል።
በባሃሩ ይድነቃቸው