የቃሊቲ የአውቶቢስ ዴፖ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆን ተገለፀ
አዲስ አበባ ፣ የካቲት 22፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የቃሊቲ የአውቶቢስ ዴፖ ግንባታ 98 በመቶ ተጠናቀቀ።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በመጠናቀቅ ላይ ያለውን ይህን የአውቶቢስ ዴፖ ዛሬ ጎብኝተዋል።
በዚህም ወቅት ዴፖው በአንድ ወር ግዜ ውስጥ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆን ተገልጿል።
5 ነጥብ 2 ሄክታር ስፋት ያለው የቃሊቲ የአውቶቢስ ዴፖ ማዕከል በውስጡ ለአውቶቢሶች በቴክኖሎጂ የተደገፈ የጋራዥ አገልግሎት ፣ የእጥበትና የነዳጅ አቅርቦት እንዲሁም ዘመናዊ የአስተዳደር ህንጻ አለው።
ግንባታው ሲጠናቀቅ በቀን እስከ 500 የሚሆኑ አውቶቢሶች በተቀላጠፈ መልኩ ከላይ የተጠቀሱ አገልግሎቶችን በዴፖው ያገኛሉ ተብሏል።
ለአውቶቢስ ዴፖው ግንባታ 789 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል።
የከተማ አስተዳደሩ ዘመናዊ ዴፖዎችን በመገንባትና የአውቶቢስ አገልግሎት ስርዓቱን ይበልጥ ነዋሪውን በሚመጥን መልኩ እንደ አዲስ ለማደራጀት እየተሰራ እንደሆነ ኢ/ር ታከለ ኡማ በጉብኝቱ ወቅት ተናግረዋል።
አዲስ አበባ ፣ የካቲት 22፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የከተማ አስተዳደሩ ከዚህ ቀደም ዘመናዊ የአውቶቢስ ስምሪት መቆጣጠሪያ ማዕከል ያካተተውን የሸጎሌ የአውቶቢስ ዴፖ ግንባታን በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት ማድረጉን ከከተማ አስተዳደሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

