አሸባሪው ህወሓትን በመደምሰስ መስዋዕትነት የከፈሉና ውድ አካላቸውን ያጎደሉ ጀግኖቻችን ተጋድሎ በታሪክ የሚወሳ ነው – ዶ/ር ይልቃል ከፋለ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ህወሓትን ለመደምሰስ በተካሄደው ጦርነት ውድ መስዋዕትነት የከፈሉና አካላቸውን ያጎደሉ ጀግኖቻችን የህልውና ዘመቻ ድል በታሪክ የሚወሳ ነው ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ተናገሩ።
ʺበሕግ ማስከበርና በሕልውና ዘመቻው የተከፈለ መስዋእትነት ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና አንድነት” በሚል መሪ ሃሳብ በዘመቻው የላቀ ሚና ላበረከቱ አካላት የእውቅና እና ምስጋና መርሃ ግብር በባህር ዳር ከተማ እየተሰጠ ነው።
በስነ ስርዓቱ ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት መላው የፀጥታ ሃይሎች በህግ ማስከበሩና በህልውና ዘመቻው ደማቸውን በማፍሰስና አጥንታቸውን በመከስከስ አገር የማጽናት ሃላፊነታቸው ተወጥተዋል።
ይሁን እንጂ አሸባሪው ህወሓት በወረራ በገባባቸው አካባቢዎች ንፁሀንን በመጨፍጨፍ፣ ሴቶችን በመድፈር ሃብት በመዝረፍና ሌሎች ክፉ ድርጊቶችን ፈፅሟል ብለዋል።
በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች በሚገኙ ማህብረሰቦች ላይም የሰብዓዊ ድጋፍ እንዳይደርሳቸው ከማድርጉም በላይ ሴቶች፣ ህፃናትና አረጋውያን ህይዎታቸው እንዲያልፍና ለከፋ ስቃይ እንዲዳረጉ ያደረገ በደል መፈፀሙን ገልፀዋል።
አሸባሪው ቡድን ይህን አሰቃቂ ድርጊት የፈፀመው ለዘመናት ተዛምዶና ተዋዶ የኖሩትን የአማራና የትግራይ ህዝቦች አንድነት በመናድ አገር ለማፍረስ የያዘውን ግብ ለማሳካት ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።
ሆኖም የመከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ክልል የፀጥታ ሃይሎችና የሌሎች ክልሎች የፀጥታ ሃይሎች ባደረጉት ቆራጥ የጋራ ተጋድሎ ቡድን ተበታትኖ እንዲመለስ መገደዱን አመልክተዋል።
በዚህ ጦርነት መስዋትነት ለከፈሉ፣ ውድ አካላቸውን ላጎደሉ ጀግኖቻችን ለዛሬው የመጀመሪያው የህልውና ዘመቻ ድል ስላበቁን በታሪክ የሚወሳ መሆኑን ገልፀዋል።
አሸባሪ ቡድኑ አሁንም ሃገር የመበተን ህዝብን የማሰቃየት ክፉ ሴራውን ዳግም ለመፈፀም እየተነሳሳ መሆኑን ጠቅሰው፤ መላ ኢትዮጵያውያን በተባበረ የጀግንነት ክንዳቸው ህልሙን በማምከን የተለመደ ትብብራቸውን እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የአስተዳደር ጉዳዮች አስተባባሪ ዶክተር ሰማ ጥሩነህ በበኩላቸው ÷በመስዋትነታችን የኢትዮጰያን አንድነት ማፅናት ተችሏል፣ አሸባሪው ቡድን በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት በመፈፀም ወደ ወረራ የገባው በስልጣን ዘመኑ ያፈረስኳት ሃገር መቼም በአንድነት አትሰለፍም ብሎ በማመኑ ነው ብለዋል።
የሽብር ቡድኑን በአንድነት ተሰልፈን በአደረግነው ቆራጥ ተጋድሎ የሃገራችን አንድነትና የህዝባችን ደህንነት መጠበቅ ችለናል ሲሉም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡