Fana: At a Speed of Life!

የ3ኛው ዙር የ8100A የታላቁ ህዳሴ ግድብ የስልክ መልዕክት የገቢ ማሰባሰቢያ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የታላቁ ህዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠበትን 9ኛ ዓመት አስመልክቶ 3ኛው ዙር የ8100A የስልክ መልዕክት የገቢ ማሰባሰቢያ በፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በይፋ ተጀምሯል።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለሀገራችን ህዝብ ኑሮ መሻሻል በአንድነት የዘመትንበት የአድዋ አምሳያ ድላችን፤ የአንድነታችን ተምሳሌት ዳግም አድዋችን ነው ብለዋል።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ግድቡ ከልማት ፕሮጀክት በላይ ዋጋ እንዳለውም ገልጸዋል።

የነገ የልማት ተስፋችንን አቅርቦ የሚያሳየን የዛሬ ድህነት ጦርና ጋሻችን ነውና ትናንት ያለንን የገበርንበትን ግድብ ዛሬም ከታሰበው ጊዜ ቀድሞ በማጠናቀቅ ድላችንን እንድገም ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

በብሄራዊ ቤተመንግስት በተካሄደው የማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የተለያዩ የጥበብ ስራዎች ቀርበዋል።

በዚህ አድዋ ነው አባይ፤ የዘመናችን ድህነትን መውጊያ ጋሻና ጦራችን ነውና ለግድቡ የቀረበው ጥሪም እንደ አድዋ የክተት አዋጅ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የምንከተለው ነው የሚል መልዕክት ተላልፎበታል።

በስነ ስነ ስርዓቱ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ፣ የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ፣ የብሄራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ ፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳውን ጨምሮ የተለያዩ እንግዶች ተገኝተዋል።

በመርሃግብሩ ላይ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ጨምሮ ከታላቁ የህዳሴ ግድብ የህዝብ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ጋር በትብብር በመስራት ከፍተኛ ድጋፍ ላደረጉ አጋር ድርጅቶች ከፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የእውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

በአክሱማዊት ገ/ህይወት

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.