Fana: At a Speed of Life!

1 ነጥብ 5 ሚሊየን ዓመት ዕድሜ ያለው የጭንቅላት ቅሪተ አካል በአፋር ክልል ተገኘ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኦልዶዋንና አሹሊያን የተሰኙ የድንጋይ መሳሪያዎች ከሆሞ ኢሬክተስ የጭኝቅላት ቅሪተ አካላት ጋር በአፋር ክልል የጎና መካነ ጥናት ተገኙ።

የጭንቅላት መጠኑ በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ከሚገኙትና ሆሞ ኢሬክተስ በመባል ከሚታወቁት የቅድመ ሰው ዝርያ አካላት አነስተኛ የሆነ የራስ ቅል ቅሬተ አካል ከተለያዩ የድንጋይ መሳሪያዎች ጋር ነው በጎና ፕሮጀክት መገኘቱ የተገለፀው።

የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ፥ በጎና የተገኙት የራስ ቅሎች ሁለት ሲሆኑ ሆሞ ኢሬክተስ በመባል በሚታወቀው የቅድመ ሰው ዝርያ የሚካተቱ መሆናቸውን አስታውቋል።

እነዚህ ቅሪተ አካላት ኦልዶዋን እና አሹሊያን ተብለው በሚጠሩት የድንጋይ ዘመን መሳሪያዎች ይጠቀሙ እንደነበር ተነግሯል።

የተገኘው የራስ ቅል የአንጎል መጠኑ (590 ሲሲ) ሲሆን፥ ይህ ግኝት ከአሁን ቀደም በሆሞ ኢሬክተስ የድንጋይ መሳሪያ አጠቃቀም የነበረንን የእውቀት አድማስ በማስፋት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋልምተብሏል።

ግኝቱ ይፋ የተደረገው ስፔን በሚገኘው የሰው ልጅ አመጣጥ ጥናት ማዕከል ተመራማሪ በሆኑት ትውልደ ኢትዮጵያዊው ዶክተር ስለሺ ሰማው እና በአሜሪካ በሳውዘርን ኮኔክቲከት ስቴት ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ ፕሮፌሰር በሆኑት ዶክተር ማይክል ሮጀርስ በሚመራው የጎና መካነ ጥናት ፕሮጀክት መሆኑም ተመላክቷል።

የመጀመሪያው በአቶ ኢብራሂም ሀቢብ የተገኘው ሙሉ የራስ ቅል 1 ነጥብ 5 ሚሊየን አመታት ዕድሜ ያለው ነው።

በሁለተኛው ግኝት በፕሮፌሰር ኒኮላስ ቶዝ በከፊል የራስ ቅል የተገኘ ሲሆን፥ እድሜው 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ዓመት ነው ተብሏል።

ይህ ግኝት ሆሞ ኢሬክተስ ሁለቱንም የድንጋይ መሳሪያ አይነቶች በአንድ ተመሳሳይ ጊዜ ሰርቶ ይጠቀም እንደነበር በጉልህ አመላካች መሆኑን ያሳያል ነው የተባለው።

ከአሁን ቀደም በሀገራችን የተገኙት የሆሞ ኢሬክተስ ቅሪተ አካላት የሚታወቁት ከመካከለኛው አዋሽ (ዲካ)፣ መልካ ቁንጡሬና ከኮንሶ ብቻ ሲሆን፥ በጎናው ፕሮጀክት የተገኘው ሆሞ ኢሬክተስ ግኝት አዲስ እና አስፈላጊ ተጨማሪ መረጃን አበርክቷል ተብሏል።

የጎና የፓሌዎአንትሮሎጂ ጥናት ፕሮጀክት ባለፉት 30 ዓመታት የምርምር ስራው በዓለም እጅግ ጥንታዊና 2 ነጥብ 6 ሚሊየን ዓመታት ያስቆጠሩ የድንጋይ መሳሪያዎችን እንዲሁም 4 ነጥብ 4 ሚሊየን ዓመታት ያስቆጠረውን አርዲፒቲከስ ራሚደስ የተባለውን ጥንታዊ ሰው ቅሪተ አካል በማግኘት በተለያዩ ዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ በማሳተም ይታወቃል።

በመሰረት ደምሱ

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.