Fana: At a Speed of Life!

ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከ6 ነጥብ 3 ቢሊየን በላይ ችግኝ ተዘጋጅቷል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዘንድሮው ለሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከ6 ነጥብ 3 ቢሊየን በላይ ችግኝ መዘጋጀቱን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።

መርሐ ግብሩ ተግባራዊ መደረጉ በየዓመቱ 92 ሺህ ሄክታር የነበረውን የደን ውድመት መጠን ወደ 32 ሺህ ሄክታር ዝቅ ማድረግ መቻሉም ተገልጿል።

የግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ኃብት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር እያሱ ኤልያስ÷ በዘንድሮው አመት በደን፣ በፍራፍሬና በደን ጥምር እርሻ መስኮች ችግኞችን ለመትከል መታቀዱን ገልጸዋል።

ለመርሐ ግብሩ የችግኝ ማፍላትና ሌሎች ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑ ገልጸው በአሁኑ ሰዓት ከ6 ነጥብ 3 ቢሊየን በላይ ችግኝ መዘጋጀቱን ነው የተናገሩት።

በመጪው ሰኔ 15 ቀን 2014 ዓ.ም የዘንድሮው ዓመት የአገራዊ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ የማስጀመሪያ መርሐ ግብር እንደሚኖርም አመልክተዋል።

በአሁኑ ወቅት ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን ክትትልና እንክብካቤ አድርጎ የጽድቀት ምጣኔውን የማሳደግ ሥራ እየተከናወነ ይገኛልም ነው ያሉት።

ከአራት ዓመት በፊት የደን መጨፍጨ ምጣኔ በዓመት ከነበረበት 92 ሺህ ሄክታር ወደ 32 ሺህ ሄክታር ዝቅ ማለቱን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት እየተተከሉ ያሉ ችግኞትን ለውጤት ማብቃት ኢትዮጵያ ለተለያዩ ሥራዎች በዓመት የምታስገባውን 4 መቶ ሚሊየን የእንጨት ውጤቶች በአገር ውስጥ ለመተካት ቁልፍ ተግባር ነው ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት የተተከሉ ችግኞች የጽድቀት ምጣኔ 84 በመቶ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ፕሮፌሰር እያሱ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሀሳብ አመንጭነት “ኢትዮጵያን እናልብሳት” በሚል መሪ ቃል ላለፉት ሦስት ዓመታት መካሄዱ ይታወሳል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.