አቶ ደመቀ መኮንን ከጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በስልክ ተወያዩ
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 9 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አነሌና ቤርቦክ ጋር በስልክ ተወያዩ።
በውይይቱ አቶ ደመቀ መኮንን ጀርመን ከኢትዮጵያ ጋር ረጅም አመታትን ያስቆጠረ ጠንካራ ወዳጅነት ካላቸው ሃገራት አንዷ መሆኗን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ፈተና ባጋጠማት ያለፈው አንድ አመት ተኩል ጊዜ የጀርመን መንግስት ሚዛናዊ አቋም ይዞ መቆየቱን የጠቀሱት አቶ ደመቀ ለዚህም ምስጋና አቅርበዋል።
በውይይታቸው በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የገጠሟትን ተግዳሮቶች ለመፍታት በመንግስት በኩል እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ከህወሓት ጋር ላለው ችግር ሰላማዊ መፍትሄን ለማምጣት መንግስት ብዙ ርቀት መጓዙን የገለፁት አቶ ደመቀ÷ ለዚህም በእስር ላይ የነበሩ የህወሓት አመራሮች መፈታታቸውን፣ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን መቋቋሙን፣ ከአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሉሴጉን ኦቦሳንጆ ጋር እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው ይህም ለሰላም ላለው ቁርጠኝነት ማሳያ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች በሚገኙ የሰብአዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የሚደርሰው እርዳታ መጠን መጨመሩን ገልጸው÷ እነዚህ መሻሻሎች መተማመንን ለመገንባት እና ዘላቂነት ያለው ሰላምን ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለው ጥረት አካል መሆናቸውን ተናግረዋል።
የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ በበኩላቸው÷ የሰብአዊ እርዳታ ተደራሽነትን ለማሳደግ፣ ተጠያቂነትን ለማስፈን እና ሁሉን አካታች የፖለቲካ ውይይት ለማካሄድ የኢትዮጵያ መንግስት እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀዋል።
የጀርመን መንግስት በሁለቱ ሀገራት መካከል የነበረውን የልማት ትብብር ከማጠናከር ባሻገር በኢትዮጵያ ሰላምን ለማረጋገጥ እና በጦርነት የወደሙ ተቋማትን መልሶ የመገንባት ስራዎች እገዛ እንደምታደርግ ገልጸዋል።
በአውሮፓ ሕብረት ውስጥ ባላት ሚናም በሕብረቱ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማደስ በሚሠሩ ሥራዎች አዎንታዊ ሚና ትጫወታለች ማለታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡