ወደ ሀገራቸው መመለስ የሚፈልጉ ፍልሰተኞችን መመለስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መወያየታቸውን በጂቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ ገለጹ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጂቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ ኢትዮጵያውያን ፍልሰተኞችን ማጠናከር እና ወደ ሀገራቸው መመለስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ኃላፊዎች ጋር ውይይት ማካሄዳቸውን ገልጸዋል፡፡
አምባሳደር ብርሃኑ የዓለም አቀፉን የፍልሰተኞች ድርጅት ኃላፊ ኢዩጌኒዮ አምብሮሲ እና በጂቡቲ የድርጅቱ ተልዕኮ አስፈጻሚ የሆኑትን ስቴፋኒ ዴቪዮት ተቀብለው ማነጋገራቸውን ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያመላከተው፡፡
አምባሳደሩ ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ከኢትዮጵያ ተነስተው በጂቡቲ ወደ የመን በማቋረጥ የፈለሱ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ያሳየውን ትብብር ማድነቃቸው ተጠቁሟል፡፡
አሁንም በድርጅቱ ፍልሰተኞችን የመመለስ መርሃ-ግብር ተጠቃሚ ሆነው ወደ ሀገራቸው መመለስ የሚፈልጉ ፍልሰተኛ ኢትዮጵያውያን እንዳሉ አምባሳደሩ ገልጸዋል፡፡
የዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ቀጣይነት ያለው ትብብሩን እንዳያቋርጥም ጠይቀዋል፡፡
የዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ዋና ኃላፊ ኢዩጌኒዮ አምብሮሲ በበኩላቸው ÷ የኢትዮጵያ መንግስት ኢትዮጵያውያኑ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀው በቀጣይም ድርጅቱ ወደ ኢትዮጵያ የሚመለሱ ፍልሰተኞችን ለመርዳት ያለውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል፡፡
በጂቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት በጥምረት ፍልሰተኞችን በመመለሱ ተግባር ላይ ለመሥራት ተስማምተዋል፡፡