Fana: At a Speed of Life!

አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በጋምቤላ ከተማ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን የሀይማኖት አባቶች ሃይማኖታዊ ተልዕኳቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ከተማ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን የሀይማኖት አባቶች ሃይማኖታዊ ተልዕኳቸውን እንዲወጡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ጥሪ አቀረቡ።

በጋምቤላ ከተማ ተከስቶ በነበረው ግጭት ዙሪያ እና በቀጣይ ዘላቂ ሰላም ማስፈን በሚቻልበት ሁኔታ ከሀይማኖት አባቶች ጋር ውይይት ተካሂዷል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በውይይቱ ወቅት እንዳሉት ፥ የሃይማኖት አባቶች የክልሉን ብሎም የሀገርን ሰላም ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ የማይተካ ሚና አላቸው ብለዋል።

መንግስት እየሰራ ያለው የሰላም ግንባታ ስራ ስኬታማ እንዲሆን የሃይማኖት አባቶች እያበረከቱት ያለውን ሚና አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

መንግስት የህዝቡን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመው ፤ በተለይ የኃይማኖት አባቶች ስለ ሰላም አስፈላጊነት ለህብረተሰቡ እየሰጡት ያለውን ግንዛቤ ሊያጠናክሩ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተንኩዌይ ጆክ በበኩላቸው ፥ የሃይማኖት መሪዎች ቅዱሳት መጽሐፍት የሚያዙትን ሠላም፣ ፍቅርና አንድነትን ለተከታዮቻቸው በማስተማር በክልሉ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

በውይይቱ ተሳታፊ የነበሩ የሀይማኖት አባቶች እንዳሉት ፥ የሃይማኖታቸው አስተምህሮ ሰላምን የሚሰብክ በመሆኑ ስለ ሰላም አስፈላጊነት ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ ጠቁመዋል።

ከከተማው የፀጥታ ሀይል ጋርም ያላቸውን ትስስር አጠናክረው በማስቀጠል የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ እንዳይስተጓጎል ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ አስረድተዋል።

በሰሞኑ በከተማው የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ የንግዱ ማህበረሰብን መንግስት ተከታትሎ አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ መጠየቃቸውን ከጋምቤላ ክልል መንግስት ፕሬስ ሴክሬታርያት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.