Fana: At a Speed of Life!

“በወጪ ምርት ዘርፍ በጣም ግዙፍ ዕመርታ ታይቷል ”- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ሁለት ዓመታት በወጪ ምርት ዘርፍ በጣም ግዙፍ ዕመርታ ታይቷል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ በተካሄደው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የወጪ ምርት እድገትን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ÷ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተሠራነው ሥራ በሸቀጦች የወጪ ምርት ከአራት ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል፡፡

ይህንን ለጥቂት ዓመታት ጠብቀን ማስቀጠል ከቻልን የወጪና ገቢ ሚዛንን ለማስጠበቅ እና የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመፍታት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በ2002 ዓ.ም ሁለት ቢሊየን ዶላር ኤክስፖርት ማድረጓን ጠቁመው÷ ከ2002 እስከ 2012 ድረስ ሦስት ቢሊየን ዶላር ለማድረስ ተቸግራ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
በአስር ዓመታት ውስጥም ቢሆን አንድ ቢሊየን ዶላር ብቻ መጨመር መቻሉን ገልጸው÷ ባለፉት ሁለት ዓመታት በሠራነው ሥራ ግን በሁለት ዓመት ብቻ ከ1 ቢሊየን ዶላር በላይ በመጨመር በሸቀጦች የወጪ ምርት ከአራት ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን አብራርተዋል፡፡
በአገልግሎት ዘርፍ ደግሞ 25 በመቶ አድገት በማሳየት ከ 6 ቢሊየን ዶላር በላይ መገኘቱን ተናግረዋል፡፡
ከሕዝብ ቆጠራ ጋር በተያያዘ በሰጡት ማብራሪያም÷ ለበጀት ብቻ ሳይሆን ለማንኛውም ስራ የሕዝብ ቆጠራ አስፈላጊ መሆኑን መውሰድ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
መሠረተ ልማትን በተመለከተም÷ ከመንገድ አኳያ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ሰፊ ሥራ መሥራቱን ገልጸዋል፡፡
በተለያየ ምክንያት የተጓተቱ የመንገድ ግንባታዎች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ ይደረጋልም ነው ያሉት፡፡
ከኤሌክትሪክ አኳያ÷ ዘርፉ መሰረተ ልማት ገንብቶ ኃይልን ማምረት፣ ማስተላለፍ፣ ማከፋፈልና ማሰራጨትን የሚያካትት መሆኑን ጠቁመው÷ የሚመረተው ኤሌክትሪክም በናሽናል ግሪድ ከማዕከል የሚሰራጭ በመሆኑ አንዱ ቦታ የሚከሰት ችግር በሌላው የሀገሪቱ ክፍል የመብራት መጥፋት እንደሚያስከትል አንስተዋል፡፡
ስለሆነም ይህን ችግር ለመቅረፍ÷ በየሥፍራው በቀጥታ ኃይል መሠራጨት እንዲችል ‘ኦፍ ግሪድ’ አሠራርን መከተል ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
ከመስኖ ልማት አንጻር÷ ለጎዴ መስኖ ከፍተኛ ትኩረት እንደተሰጠው ገልጸው፥ ሥራው አድካሚ ቢሆንም ሲጠናቀቅ መስኖው ከፍተኛ ሥራ መሥራት ያስችላል ብለዋል፡፡
ስኳርን በተመለከተም÷ አምስት ተጨማሪ የስኳር ፋብሪካዎች መጨመራቸውን ጠቁመው÷ ከዚሁ ጋር በተያያዘም የሀገር ውስጥ ፍጆታዎችን ያማከለ የአገዳ ምርት ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡
ከወደብ ጋር በተያያዘም ስምንት ደረቅ ወደቦች መኖራቸውን እና ይህንኑ ቁጥር ወደ 11 ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
ኢትዮጵያ ካላት የሕዝብ ብዛት አንኳያ ወደቦች የግድ አስፈላጊ መሆናቸውን በማብራሪያቸው አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የወጪና ገቢ ንግድ መሳለጥ እንደሚገባው አመልክተው÷ ለዚህም የሎጂስቲክ ሥርዓቱን የማዘመን ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
በዚህ ዓመት 98 በመቶ የቡና ምርት በኮንቴይነር መላኩንም ለአብነት አንስተዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.