Fana: At a Speed of Life!

ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ ሄዶ ኮሮና ቫይረስ ተገኘበት የተባለው ግለሰብ ወደ ሀገሪቱ ከተመለሰ ሳምንታትን ያስቆጠረ መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ ሄዶ ኮሮና ቫይረስ ተገኘበት የተባለው ግለሰብ ወደ ሀገሪቱ ከተመለሰ ሳምንታትን ያስቆጠረ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የጤና ሚኒስትር ደኤታ ዶክተር ሊያ ታደሰ ከትናንት ጀምሮ በማህበራዊ ድረ ገፆች እየተሰራጨ ያለው እና ከኢትዮጵያ እንደ ሄደ ቫይረሱ ተገኘበት በተባለው አሜሪካዊ ጉዳይ ዙሪያ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዚህም መረጃወን የማጣራት ሰራ እየሰራን ነው ያሉት ዶክተር ሊያ፥ ግለሰቡ ኢትዮጵያ መጥቶ የነበረ ቢሆንም ወደ አሜሪካ ከተመለሰ ግን ሳምንታትን ማሳለፉን ከኤምባሲ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳይ ተናግረዋል።

ዶክተር ሊያ ታደሰ በማከልም፥ የኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ የጤና ሚኒስቴር የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ የእለት ተእለት ተግባሩ አድርጎ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

እስካሁን ከተለያዩ የአለም ሀገራት የመጡ 278 ሺህ መንገደኞች በሙቀት መለኪያ እንዲያልፉ መደረጉን አስታውቅዋል።

ከእነዚህም ወስጥ የቫይረሱ ምልክት ይሆናሉ ተብለው አጠራጠሪ ነገሮች የታዩባቸው 39 መንገደኞች በለይቶ ማቆያ ማእከል እንደገቡ በማድረግ ናሙናቸው ተወስዶ ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸው ተረጋግጧል።

በአሁኑ ሰአት ከቻይና በተጨማሪ እንደ ጣሊያን፣ ኢራን፣ ደቡብ ኮሪያ እና የመሳሰሰሉ ሀገራት የሚመጡ መንገደኞች ላይ ተጨማሪ ክትትሎች እየተደረገ መሆኑን ነው ሚኒስትር ደኤታዋ ያነሱት።

ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሀገራት የሚመጡ መንገደኞችንም ቅፅ በማስሞላት እና አድራሻቸውን በመያዝ በስልክ ተጨማሪ ክትትሎች እየተደረገላቸው መሆኑን በማከል።

በዚህ መንገድ እስካሁን ከተለያዩ ሀገራት የመጡ 1 ሺህ 20 መንገደኞች ተጨማሪ ክትትል የተደረገላቸው ሲሆን፥ 1 ሺህ 93 መንገደኞች ደግሞ በስልክ ከትትል እየተደረገላቸው የሚገኙ ናቸው ብለዋል።

የሙቀት መጠናቸው ላይ ጥርጣሬ የታየባቸው ሶስት መንገደኞችም በለይቶ ማቆያ ውስጥ ክትትል ላይ መሆናቸውን ዶክተር ሊያ ተናግረዋል።

ሚኒስቴሩ ቫይረሱ ቢከሰትም በፈጥነት መቆጣጠር የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እያከናወነ ሲሆን፥ የሆስፒታል ዝግጅት፣ የግብአት እና የባለሙያዎች ዝግጅትም በስፋት እየተሰራበት ነው።

የኮሮና ቫይረስ በብዛት ጉንፋን መሰል ምልክቶችን የሚያሳይ እና የመተንፈሻ አካላትን የሚያጠቃ ቫይረስ ስለሆነ ህብረተሰቡም ጥንቃቄዎችን ማድረግ ላይ መዘናጋት አንደሌለበት ነው ዶክተር ሊያ የነተናገሩት።

በሚሰራጩ መረጃዎች ህብረተሰቡ ሳይደናገጥ መረጃዎች ትክክለኛ መሆናቸውን በማረጋገጥም የበኩሉን ደርሻ እንዲወጣ ያሳሰቡት ዶክተር ሊያ፥ በተለይም የግል ንፅህናን መጠበቅ እና ንክኪዎችን መቀነስ ላይ ትኩረት ማደረግ አለበትም ብለዋል።

ህብረተሰቡ የሚያጠራጥሩ ነገሮችን ሲመለከትም ሆነ መረጃዎችን እና እርዳታዎቸን ለማግኘት ወደ 8335 መደወል አንዳለበትም ገልፀዋል።

በዙፋን ካሳሁን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.