የመዲናዋ አስተዳደር በ2014 በጀት ዓመት ማጠቃለያ እና በ2015 የዝግጅት ምዕራፍ ሥራዎች ላይ እየተወያየ ነው
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2014 በጀት ዓመት ማጠቃለያ እና የ2015 የዝግጅት ምዕራፍ ሥራዎች ግምገማ እና ውይይት እየተካሄደ ነው።
መድረኩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፣ በብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መለስ ዓለሙ እና ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር ዓባይ በተገኙበት ነው የተጀመረው፡፡
ለሦስት ቀናት በሚቆየው የከተማዋ ከፍተኛ አመራሮች የሚሳተፉበት መድረክ÷ የ2014 የመንግሥትና የፓርቲ ሥራ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2015 የትኩረት ነጥቦች ላይ ውይይት እንደሚደረግ የከንቲባ ጽሕት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡
በከተማዋ ከተከናወኑ በርካታ ተግባራት መካከል በጥንካሬ ትምህርት የሚወሰድባቸውን በመለየት የማስፋት እና ቀጣይነቱን የማረጋገጥ ሂደት ላይ በትኩረት ውይይት እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡
እዲሁም ባለፈው በጀት ዓመት የነበሩ እጥረቶችን እና ጉድለቶችን በመለየት የመሙላትና የእርምት እርምጃ መውሰድ የሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይም ውይይት እንደሚደረግ ይጠበቃል፡፡
በተጨማሪም በቀጣይ በጀት ዓመት ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት በመፍጠር የከተማዋን ልማትና ዕድገት ለማፋጠን፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማቃለል፣ አንገብጋቢ የሕዝብ ጥያቄዎችን ለመፍታት እና የኑሮ ጫናውን መቀነስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በመምከር በትኩረት እንደሚሠራ ተመላክቷል፡፡