Fana: At a Speed of Life!

ቢሮው በተለያዩ የቴክኒክና ሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን ከ10 ሺህ በላይ ተማሪዎች አስመረቀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ስልጠናና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን ከ10 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ዛሬ አስመርቋል።

ቢሮው÷ ከደረጃ 2 እስከ ደረጃ 5 በ124 የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ነው ያስመረቀው።

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አበቤ፣ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል፣ በብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መለስ ዓለሙን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ተመራቂዎች ያገኙትን ክህሎት እና እውቀት ተጠቀመው ለኢንዱስትሪ ልማቱ እድገት የሚጠበቅባቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ልማታችንን ለማጠናከር የኢትዮጵያ ተስፋዎችን አብቅተናል ያሉት ከንቲባ አዳነች÷ የስራ ባህሉ የዳበረ አምራች ኃይል እንዲኖር የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች እያደረጉት ያለው ጥረት ከፍተኛ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

ከተማችን ከተመራቂዎች ብዙ ተስፋ ስላላት÷ በተለይ የውጪ ምንዛሬ ወጭ በመቀነስ ረገድ ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ በማምረት የገበያ ክፍተትን ለመሙላት መረባረብ ይገባል ብለዋል፡፡

ለእዚህም ከተማ አስተዳደሩ ለዘርፉ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው የተናገሩት።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.