የኢትየጵያን ብሔራዊ ደህንነት ለማስጠበቅ ከግል ፍላጎት ይልቅ ሀገርን ያስቀደሙ ስራዎችን መስራት ይገባል- ምሁራን
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትየጵያን ብሔራዊ ደህንነት ለማስጠበቅ ከግል ፍላጎት ይልቅ ሀገርን ያስቀደሙ ስራዎችን መስራት እንደሚገባ ምሁራን ተናገሩ፡፡
የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁራኑ እንደተናገሩት የውስጥ አንድነት መሸርሸር የውጭ ተጋላጭነትን የሚጨምር በመሆኑ ከሚጥሉ አጀንዳዎች መቆጠብ ይገባል፡፡
የፖለቲካ ሳይንስና ዴሞክራሲ ምሁሩ ዶክተር ሀይለየሱስ ታዬ ብሔራዊ ደህንነት የመንግስት ቀዳሚ ስራ መሆኑን አንስተው ነግር ግን ጉዳዩ የሁሉም ዜጋ ሃላፊነት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁሩ ረዳት ፕሮፌሰር ዳምጠው ተሰማ በበኩላቸው በታሪክ ኢትዮጵያ የውስጥ አንድነቷ የተዳከመ ሲመስላቸው የውጭ ጠላቶች ፈተናዎችን ሲሰነዝሩ መቆየታቸውን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ፈተናዎችን በጋራ ክንድ መመከታቸውን ያወሱት ረዳት ፐሮፌሰሩ ዛሬም አንድነትና አብሮ መቆም እንደሚያስፈልግ አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የምትገኝበት የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና የሀያላን ትኩረትና የተለያየ ፍላጎት ያለበት መሆኑን በማንሳትም ይህ ፍላጎታቸው በሀገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት እንዲያንፀባርቁ አደርጓል ነው ያሉት፡፡
የምስራቅ አፍሪካን ክፍለአህጉር ትስስር ማጠናከርም በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡
በአፈወርቅ እያዩ