Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ ከ17ሺ በላይ የክላሽ እና የሽጉጥ ጥይት ከተለያዩ የጦር መሳሪያዎች ጋር ተያዘ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2014 (ኤፍ ቤ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በህግ ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ የተገኘ ከ17 ሺህ በላይ የክላሽ እና የሽጉጥ ጥይት ከተለያዩ የጦር መሳሪያዎች ጋር መያዙን ፖሊስ አስታወቀ፡፡
 
ህገ ወጥ መሳሪያዎቹ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ልዩ ቦታው ሃና ማርያም አካባቢ በቶዮታ ተሽከርካሪ ሲጓጓዙ ነው የአዲስ አበባ ፖሊስ እና የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ባደረጉት ክትትል የታየዙት፡፡
 
በዚህም 11 ሺህ 275 የክላሽ ጥይት፣ 6 ሺህ 494 የሽጉጥ ጥይት፣ 11 የተለያዩ መሳሪያዎች ፣ በባለሙያ የተፈታቱ 9 የብሬን ሰደፍ፣ 4 የብሬን ተመላላሽ ሽቦ፣ 6 የብሬን ተመላላሽ ዘንግ፣ ልዩ ልዩ የክላሽ ኮቭ ጠብመንጃ አካሎች ፣ ዝናር ፣ ብዛቱ 37 የሽጉጥ ካርታ ከሌሎች የጦር መሳሪያዎች ጋር መያዛቸው ተመላክቷል፡፡
 
ከዚህ ባለፈም በሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3-B-01563 አ/አ ቶዮታ ሎንግ ቤዝ በሆነ ተሽከርካሪ 465 የስታር ሽጉጥ ጥይት እና 1 ኢኮልፒ ሽጉጥ መያዙን ከአዲስ አበባፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
 
የጦር መሳሪያዎቹን ሲያዘዋውሩ የተገኙት ሶስት ተጠርጣሪዎች ተይዘው ምርመራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ነው የተገለጸው፡፡
 
ተቋማቱ ከዚህ በፊት ባደረጉት የጋራ ቅንጅታዊ ስራ ለከተማዋ ሰላምና ደህንነት ከፍተኛ ስጋት የሆኑ ተቀጣጣይና ተተኳሽ የጦር መሳሪያዎችና ጥይቶችን በቁጥጥር ስር ማድረጋቸው የሚታወስ ነው፡፡
 
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከልዩ ልዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ወደ አዲስ አበባ ከተማ የሚገባው ህገ ወጥ የጦር መሳሪያና ጥይት ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ፖሊስ አስታውቋል፡፡
 
የህዝብ የነቃ ተሳትፎ ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ መሰረት በመሆኑ መሰል ህገ ወጥ ተግባራት ሲመለከት ለሚመለከተው አካል ጥቆማ በመስጠት ቀና ተባባሪነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀርቧል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.