“ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የምክክር ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንጂ የማደራደር ሥልጣን የለውም”-የኮሚሽኑ ሰብሳቢ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) “የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ኃላፊነት በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የምክክር መድረክ ማመቻቸት እንጂ የማደራደር ሥልጣን የለውም” ሲሉ የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን ዓርዓያ ተናገሩ።
ኮሚሽኑ ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ገቢራዊ በሚያደርገው ስትራቴጂክ ዕቅድ ዙሪያ ከብዙሃን-መገናኛ ፣ከሠላም ሚኒስቴር፣ ከሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና ከሌሎች ባለድርሻ ሲቪክ ተቋማት ተወካዮች ጋር ተወያይቷል።
የምክክር ኮሚሽኑ የተቋቋመው በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ በተፈጠሩ ልዩነቶች በውይይት ዘላቂ ዕልባት መስጠት የሚያስችሉ ህዝባዊ ምክክሮችን በማካሄድ ችግሮችን ለይቶ በጥናት የተደገፈ መፍትሄ ለማመላከት ነው ተብሏል።
ለዚህም አካታችና አሳታፊ፣ ገለልተኛ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት፣ ትብብር፣ ሕጋዊነትና ተዓማኒነትን መሰረት ያደረገ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑም የምክክር ኮሚሽኑ ሰብሳቢ ፕሮፈሰር መስፍን አርዓያ ገልፀዋል።
ኮሚሽኑ ግቡን ለማሳካት ይረዳው ዘንድም ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ማዘጋጀቱን ገልጸው፤ ለምክክሩ ውጤታማነትም ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርቦ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በምክክር ሂደቱ አጀንዳ የመቅረጽ ኃላፊነት ለህዝብ የተተወ መሆኑን ገልፀው፤ ኮሚሽኑ የህዝብ አጀንዳዎች ተቀባይነት እንዲያገኙ ይሰራል እንጂ የህዝቡ አጀንዳ የመቅረጽ ኃላፊነት እንዳልተሰጠው ተናግረዋል።
ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የውይይት ሂደቶችን ማመቻቸት እንጂ የማደራደር ሥልጣን የለውም ብለዋል።
በተሰጠው ማብራሪያ ላይ ተሳታፊዎች ቢካተቱ በሚሏቸው ጉዳዮች ላይ ሀሳብ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ከተሳታፊዎች መካከል ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች አገሪቷ ያለፈችበትን ውጣ ውረድ በቅርበት እንደሚያውቁ በመግለጽ ሚዲያዎችን ማሳተፍ ለምክክሩ ስኬት የጎላ ፋይዳ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።
ከኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌደሬሽን የተወከሉት አቶ ጌቱ ሙላቱ፤ ምክክር ኮሚሽኑ የአካል ጉዳተኞችን ማሳተፍ ላይ የበለጠ መስራት እንዳለበት አመልክተዋል።
የአካል ጉዳተኝነት በዓይነትም፣ በአደረጃጀትም የተለያዩ በመሆናቸው ኮሚሽኑ ይህን ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ሁኔታዎችን እንዲያመቻችም ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ተወካይ ዶክተር መብራቱ ዓለሙ በበኩላቸው ኮሚሽኑ በምክክር ላይ የቀደመ ልምድ ካላቸው ተቋማት ጋር ተቀራርቦ መስራት እንዳለበት ማንሳታቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!