ሚኒስቴሩ በዓለም አቀፉ ኢንተርኔት አስተዳደር ጉባኤ ዙሪያ ከተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ጋር ውይይት አካሄደ
አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 23 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በ17ኛው የዓለም አቀፉ የኢንተርኔት አስተዳደር ጉባኤ ዝግጅት ዙሪያ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር በለጠ ሞላ ከተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱም እስካሁን በኮሚሽኑና በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በጋራ የተከናወኑ ተግባራት ስኬትና ያሉበት ደረጃን በተመለከተ በኮሚሽኑ ከፍተኛ ኃላፊዎች ማብራርያ ቀርቧል፡፡
አጣዳፊና የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች ትኩረት በሚፈልጉ ጉዳዮች ላይም ውይይቱ የተደረገ ሲሆን÷ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በኩል ዝግጅቱን በተመለከተ የተከናወኑ አንኳር ጉዳዮች ላይ ገለጻ ተደርጓል፡፡
ኢትዮጵያ ለጉባኤው ስኬት ከመቼውም የበለጠ ቁርጠኛ ናት ያሉት ዶ/ር በለጠ÷ለጉባኤው መሳካት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሆነ መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የዓለም አቀፉ የኢንተርኔት አስተዳደር ጉባኤ ከህዳር 19 ቀን እስከ ህዳር 23 ቀን፣ 2014 በአዲስ አበባ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የመሰብሰቢያ አደራሽ ይካሄዳል፡፡