አልሸባብ ላይ የተወሰደው እርምጃ ሥኬታማ እንደነበር የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ገለጹ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሸባሪው አልሸባብ ላይ የተወሰደው እርምጃ ስኬታማ ነበር ሲሉ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሁመድ ተናገሩ ።
ርዕሰ መስተዳድሩ ይህን ያሉት በ6ኛው የሶማሌ ክልል ምክር ቤት 2ኛ ዓመት 3ኛ ዙር መደበኛ ስብሰባ ላይ የክልሉን የ2014 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ነው።
ርዕሰ-መስተዳድሩ በሪፖርታቸው ÷ በክልሉ ሰላምና ፀጥታ ለማረጋገጥ የተሰሩ ስራዎችን፣ በተለይም አሸባሪውን አልሸባብ ለመደምሰስ የተወሰደውን ከፍተኛ እና የተቀናጀ እርምጃ አቅርበዋል፡፡
የክልሉ ልዩ ኃይል የአልሸባብን የጥፋት ተልዕኮ ማክሸፍና በሽብር ቡድኑ ላይም ከፍተኛ ኪሳራ ማድረስ መቻሉን በሪፖርታቸው ላይ ገልፀዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በፍትኅ ተቋማት የተሰሩ ስራዎችን የዘረዘሩ ሲሆን በተያዘው ዓመት በ681 ዐቃብያነ ኅጎች ላይ የአሰራር ሥነ-ምግባር ግምገማ ተደርጎ የዕርምት ውሳኔዎች መሰጠታቸውንም አመላክተዋል፡፡
በተጨማሪም በፖሊስና በማረሚያ ተቋማት ላይ የታራሚዎች የአያያዝ ሁኔታ መፈተሻቸውን ጠቅሰው ያለ በቂ ማስረጃ የታሰሩ 180 የሕግ ታራሚዎች መፈታታቸውንም ነው የገለጹት።
አቶ ሙስጠፌ 224 ታራሚዎች በምሕረት መለቀቃቸውን ፣ 3 ሺህ 58 የክስ የምርመራ መዝገቦች ታይተው 2 ሺህ 756ቱ ውሳኔ ማግኘታቸውንና 302ቱ በሒደት ላይ መሆናቸውን ለምክር ቤቱ በሪፖርታቸው አቅርበዋል።
በጤናው ዘርፍ ÷ በበጀት ዓመቱ ለሁለት ሆስፒታሎች ዕድሳት፣ ለ50 ጤና ጣቢያዎች የውሃ መሰረተ ልማት የማሟላት ስራ ፣ ለ21 ጤና ጣቢያዎች የሕክምና ቁሳቁስ የሟሟላት ሥራ፣ ለአምስት ሆስፒታሎች በ35 ሚሊየን ብር የዕቃ ግዢ መከናወኑንም ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በክልሉ በተከናወነው የኮቪድ19 የክትባት ዘመቻ 3 ሚሊየን 18 ሺህ 222 ሰዎችን መከተብ መቻሉን አስረድተዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም በድርቁ የተጎዱ የቤት እንስሳትን ለመታደግ በተሰራው ስራ 321 ሺህ 640 ዕስር የእንሰሳት መኖ፣ 32 ሺህ ኩንታል የተመጣጠነ መኖ ለ89 ወረዳዎችና ከተማ መስተዳድሮች መዳረሱን እና 3 ሚሊየን 504 ሺህ 600 የቤት እንስሳት መከተብ መቻሉንም በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል።
በቀጣይ ቀናት በ6ኛው የሶማሌ ክልል ምክር ቤት 2ኛ ዓመት 3ኛ ዙር መደበኛ ስብሰባ ላይ የተለያየ አጀንዳዎች ተነስተው የተለያዩ አዋጆችና ሹመቶች ይጸድቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የክልሉ ብዙኃን መገናኛ ዘግቧል።