ወጋገን ባንክ በ2014 በጀት ዓመት አጠቃላይ አፈፃፀም 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ትርፍ አስመዘገበ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ወጋገን ባንክ ከነበረበት ዝቅተኛ አፈፃፀም በመውጣት በ2014 በጀት ዓመት አጠቃላይ አፈፃፀም 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ትርፍ ማስመዝገቡን አስታወቀ፡፡
ባንኩ ይህንን ውጤት ማስመዝገብ የቻለው የባንኩ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት፣ ባለአክሲዮኖች፣ ማኔጅመንትና ሰራተኞች ባከናወኑት የተቀናጀ ርብርብ መሆኑን የባንኩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አክሊሉ ውበት አስታውቀዋል፡፡
ባንኩ ያስመዘገበው ትርፍ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተከሰተው አለመረጋጋት በክልሉ ያሉት 112 ቅርንጫፎች አሁንም ድረስ ተዘግተው ባሉበትና በ288 ቅርንጫፎቹ ብቻ አገልግሎት እየሰጠ ከመሆኑ አንፃር ትልቅ እምርታ መሆኑን አቶ አክሊሉ ተናግረዋል፡፡
የባንኩ ጠቅላላ ሀብትም ባለፈው በጀት ዓመት ከነበረበት 40 ቢሊየን ብር ወደ 43 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ማደጉንም አያይዘው ገልፀዋል፡፡
እንዲሁም የባንኩ የተከፈለ ካፒታል 3 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር መድረሱንና ጠቅላላ ካፒታሉም 6 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር የደረሰ መሆኑን ነው ያነሱት፡፡
ወጋገን ባንክ በመላ ሀገሪቱ 400 ቅርንጫፎች እና ከ5 ሺህ በላይ ሠራተኞች ያሉት ሲሆን፥ በአሁኑ ወቅትም የባለ አክሲዮኖቹ ቁጥር 5 ሺህ 888 የደረሰ መሆኑ ተመላክቷል፡፡