Fana: At a Speed of Life!

ምድረ በዳውን መሬት ወደ ደንነት የቀየረው ቱርካዊ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ቱርካዊው ሂክመት ካያ 30 ሚሊየን ችግኞችን በመትከል ምድረ በዳውን መሬት ወደ ደንነት መቀየር ችሏል፡፡

ቫይራል ባንዲት በተባለ መጽሄት ላይ በህትምት የወጣው ጽሑፍ እንደሚያስረዳው÷ ግለሰቡ ከቱርክ የደን አስተዳደርነት በጡረታ ቢገለልም በስራ ዘመኑ ባዳበረው ክህሎት የመንደር ነዋሪዎችን በማስተባበር በሲኖፕ ከተማ አቅራቢያ 30 ሚሊየን ችግኞችን መትከል ችሏል፡፡

ችግኞችን ከተከለ በኋላ ለ19 ዓመታት እንክብካቤ ሲያደርግ የቆየው ሂክመት÷ችግኞቹን ወደ ዛፍነት በመቀየር ምድረ በዳ የነበረችውን የሲኖፕ ከተማ ወደ ልምላሜ ቀይሯታል ነው የተባለው፡፡

የደን ልማቱን ከጀመረ 41 ዓመት በኋላ ወደ አካባቢው የተመለሰው ግለሰቡ በፊት በረሀማ የነበረውን ስነ-ምህዳር ወደ ደን መቀየር መቻሉን በያዛቸው ምስሎች ያረጋገጠ ሲሆን÷ይህን በማድረጉ ኩራት እንደሚሰማው  ገልጿል፡፡

በደን ልማት ዙሪያ በአላማ ጠንክሮ መሥራት ትልቅ ጥቅም እንደሚያስገኝ ያረጋገጠው ሂክመት በቱርክ ተፈጥሯዊ መናፈሻዎችን በማዘጋጀት ረገድ ጥሩ ምሳሌ ሆኗል ነው የተባለው፡፡

እንደ ወርልድ ፎረስት ዘገባ ቱርክ በፊት የነበራት አጠቃላይ የደን ሽፋን በ5 ነጥብ 4 በመቶ የቀነሰ ሲሆን÷ የደን መጨፍጨፍ ለዚህ ዋነኛ ምክንያት ነው ተብሏል፡፡

የደን ጭፍጨፋን ለመዋጋት መንግስት ትኩረት የሚሰጥ ከሆነ ዜጎች ስለ አካባቢያዊ ስነ ምህዳር እውቀት እንዲኖራቸው ግንዛቤ የሚፈጥር መሆኑና የደን ጭፍጫፋን ለመከላከልም ሚና እንደሚኖረው ተመላክቷል፡፡

አሁን ላይም እንደ ጋና ፣ቻይና እና ህንድ የመሳሰሉ ሀገራት ችግኝ በመትከል ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን ቫይራል ባንዲት አስነብቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.