በኦሮሚያ ክልል ከ21 ሺህ በላይ የአቅመ ደካማ ቤቶችን ለመገንባትና ለማደስ እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በክልሉ ከ21 ሺህ በላይ የአረጋውያንና አቅመ ደካማ ቤቶችን ለማደስና አዲስ ለመገንባት እየተሠራ መሆኑን የኦሮሚያ ሴቶችና ህሕጻናት ጉዳይ ቢሮ አስታውቋል፡፡
የቢሮው ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ ሰርካለም ሰቡ ቤቶቹ የሚታደሱትና የሚገነቡት በሁሉም የክልሉ የገጠርና የከተማ ቀበሌዎች መሆኑን ጠቁመው÷ 7 ሺህ 500 ቤቶች አዲስ ለመገንባትና 14 ሺህ ቤቶችን ለማደስ አቅደው ወደ ሥራ መግባታቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።
በሥራውም÷ 21 ሺህ 500 የሚሆኑ አረጋውያን፣ አቅመ ደካሞች፣ አካል ጉዳተኞችና በችግር ውስጥ ያሉ እናቶች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልጸው÷ የእስካሁኑ አፈፃፀምም 50 በመቶ ላይ መድረሱን ተናግረዋል፡፡
በክልል ደረጃ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ለሚሆኑ የችግረኛ ቤተሰብ ልጆች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት÷ በመንግሥት ሊወጣ የሚችል 2 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ለማስቀረት ግብ በማስቀመጥ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው÷ የመሥራት አቅም ላላቸው ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ቀሪ ዕድሜያቸውን በደስታ እንዲያሳልፉ የማብቃት ጉዳይ ቀዳሚ አጀንዳ ነው ብለዋል፡፡
በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ክስተቶች በከፋ ችግር ውስጥ ያሉ ወገኖችን የመታደግ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመው÷ “ወቅቱ ሁሉም እረፍት የሚያደርግበት ሳይሆን ለሥራ የሚነሳበት ጊዜ ሊሆን ይገባል” ብለዋል፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!