ወንጀለኞችን ወደ አዲስ አበባ ለማስገባት እና ከሀገር ለማስወጣት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ
አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 27 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ አዲስ አበባ ወንጀለኞችንና አሸባሪዎችን ለማስገባት እና በህገወጥ መንገድ ከሀገር ለማስወጣት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከንቲባ ፅህፈት ቤት የፀጥታ ዘርፍ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር በጋራ በመሆን ሲያካሂዱ በቆዩት የክትትል ስራ መሆኑን የፅህፈት ቤቱ መረጃ ያመላክታል።
በአራዳ ክፍለ ከተማ ከሊፋ ህንፃ አካባቢ ሲደረግ በቆየው ክትትል በቁጥጥር ስር በዋሉት ግለሰቦች መኖሪያ ይህንን ተግባራቸውን ለማሳካት የተለያዩ ህገወጥ መታወቂያዎችን በመስራት፥ የፌደራል መመንግስት ሰነዶችና ማህተሞችን በማዘጋጀት፣ የጉዞ ሰነዶችን ማዘጋጀት እንዲሁም ዶላሮችን በእጃቸው ይዘው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 6 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች ፀጋዬ ካሳ፣ እስክንድር መላኩ፣ ሰይድ አሊ፣ ገሸና ገልገሉ፣ እድሪስ አደም፣ አቡበከር አህመድ የሚባሉ ናቸው፡፡
በግለሰቦቹ መኖሪያ ቤት በተደረገ ምርመራ በግለሰቦቹ እጅ 2 ሺህ 200 የአሜሪካ ዶላር፣ የተለያዩ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር የነዋሪዎች መታወቂያ፣ ከአማራ ክልል እንደተላከ በማስመሰል የሚሰሩ መሸኛ፣ በጅምር ስራ ያላለቀ የአዲስ አበባ መታወቂያ፣ ለተለያዩ ህገወጥ ህትመት መስሪያ የህትመት መሳሪያና ቀለሞች፣ የአዲስ አበባ COC ምዘና ማዕከል ሰነድ፣ የተለያዩ ፖስፖርቶች፣ ሀሰተኛ የልደት ሰርተፊኬት፣ የተለያየ ከለር ያላቸው ለህገወጥ ህትመት የሚጠቀሙበት ብዛት ያለው ወረቀቶች፣ የተለያዩ የሀሰት የጉዞ ሰነድ፣ የተለያዩ የግል ተቋማት ሀሰተኛ ማህተም ያለበት ደብዳቤ ተገኝተዋል፡፡
ፖሊስ ግለሰቦቹን በቁጥጥር ስር በማዋል ተጨማሪ የምርመራ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡