የደቡብ ምዕራብ ክልል የ2015 በጀት 11 ነጥብ 33 ቢሊየን ብር ሆኖ ጸደቀ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት ለ2015 በጀት ዓመት የቀረበውን 11 ነጥብ 33 ቢሊየን ብር በጀት አጸደቀ፡፡
የክልሉ ፉይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ወሰነች ቶማስ÷ በጀቱ በኢኮኖሚው ውስጥ መዋቅራዊ ለውጥ ለማስመዝገብ፣ የግሉን ዘርፍ ኢንቨስትመንት ለማጠናከርና የክልሉን ነዋሪዎች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚያግዝ መልኩ የተሰናዳ መሆኑን አስረድተዋል።
የማህበራዊ አገልግሎቶችን ለማስፋት የገጠርና ከተማ የስራ እድል ፈጠራዎችን በማስፋት፣ ወጣቶችን በይበልጥ ተሳታፊ የሚያደርግ ምጣኔ ሃብታዊ ባለቤትነትን የሚያረጋግጥ እንዲሆን መታለሙንም ገልጸዋል ።
የዓመቱ በጀት ምንጮች ከፌደራል መንግስት ድጎማ፣ ከድጋፍ ሰጪ አካላትና ከክልሉ ገቢ የሚገኙ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡
እስከአሁን የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ባለመከናወኑ የፌደሬሽን ምክር ቤት የሀብት ድልድሉን ማድረግ ስለማይችል፣ ከፌደራል መንግስት የሚገኘውን ድጎማ ከደቡብ ክልል 19 ነጥብ 4 በመቶ የክልሉን ድርሻ ተቀብሎ ሥራ ላይ እንደሚያውልም ነው የተጠቆመው።
በዚህም ከፌደራል መንግስት ድጎማ ፣ ከድጋፍ ሰጪ አካላትና ለዘላቂ ልማት የሚውለው በጀት ድምር 6 ነጥብ 7 ቢሊየን፣ ከክልሉ ገቢ 4 ነጥብ 1 ቢሊየን፣ በጥቅሉ የ2015 ረቂቅ በጀት 11 ነጥብ 33 ቢሊየን ሆኖ ቀርቧል።
የክልሉ ምክር ቤትም በቦንጋ ከተማ እያካሄደ በሚገኘው ስድስተኛ ዙር አንደኛ ዓመት ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ የቀረበውን ረቂቅ በጀት መርምሮ በሙሉ ድምፅ አጸድቋል።
በበርናባስ ተስፋየ