እስካሁን ለትግራይ ክልል 240 ሺህ 73 ሜትሪክ ቶን ምግብ እና 2 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ተልኳል – ኮሚሽኑ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ለትግራይ ክልል ከሐምሌ ወር 2013 ዓ.ም ጀምሮ 240 ሺህ 73 ሜትሪክ ቶን ምግብ እና 2 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር መላኩን የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ በትግራይ ክልል ችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች የሚደረገው አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
በዚህ መሰረትም ከሐምሌ ወር 2013 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ድረስ 240 ሺህ 73 ሜትሪክ ቶን ምግብ እና 52 ሺህ 645 ሜትሪክ ቶን ምግብ ነክ ያልሆኑ ግብዓቶች በክልሉ ችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች መሰራጨታቸውን ተናግረዋል፡፡
ለስራ ማስኬጃ እና ለተለያዩ አገልግሎቶችም 2 ነጥብ 9 ቢሊየን በላይ ጥሬ ብር ወደ ትግራይ ክልል መላኩን ነው የገለጹት፡፡
ከዚህ ባለፈም 1 ሚሊየን 749 ሺህ 722 ሊትር ነዳጅ፣ 258 ሜትሪክ ቶን መድሓኒት እና 7 ሺህ 257 ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ በየብስ እና አየር ትራንስፖርት ወደ ክልሉ መላኩን አብራርተዋል፡፡
እስካሁን 6 ሺህ 631 የሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሳች ወደ ትግራይ ክልል መግባታቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ፥ ከእነዚህ ውስጥም 4 ሺህ 599 ተሽከርካሪዎች የተመለሱ ሲሆን 2 ሺህ 32 የሚሆኑት ደግሞ አለመመለሳቸውን ጠቁመዋል፡፡
አቶ ደበበ በትግራይ ክልል በአሁኑ ወቅት 96 የሚሆኑ የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅቶች ችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች አስፈላጊውን እርዳታ እያሰራጩ እንደሚገኙ አንስተዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ