በመሬት መንሸራተት ምክንያት ተዘግቶ የነበረው የጋምቤላ-አዲስ አበባ መንገድ አገልግሎት መስጠት ጀመረ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በመሬት መንሸራተት ምክንያት ተዘግቶ የነበረው ጋምቤላን ከአዲስ አበባ የሚያገናኘው የአስፓልት መንገድ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የጅማ ዲስትሪክት አስታወቀ።
የዲስትሪክቱ የራስ ኃይል የመንገድ ጥገና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር መሰረት ደጀኔ እንዳሉት÷ የአስፓልት መንገዱ “ኩላሊቴ ተራራ” ተብሎ የሚጠራ አካባቢ ከጳጉሜን 4 ቀን ጀምሮ በአካባቢው የጣለው ከባድ ዝናብ ባስከተለው የመሬት መንሸራተት ምክንያት ተዘግቶ ቆይቷል ።
የተከሰተውን ችግር ለመፍታትም ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ ቆይቶ በዛሬው ዕለት ከቀኑ 6 ሰዓት ከ30 ጀምሮ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል ነው የተባለው፡፡
አሁን ላይ ማሽነሪዎችን በማስገባት መንገዱ ለአገልግሎት እንዲበቃ ማደረጉን የጠቆሙት ኢንጂነር መሰረት ሙሉ በሙሉ መንገዱን ክፍት ለማድረግ ከ10 እስከ 15 ቀናት እንደሚፈጅ መግለጻቸውን ከጋምቤላ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡