Fana: At a Speed of Life!

በፍኖተሰላም በ140 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነቡ መሰረተ ልማቶች ተመረቁ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በምዕራብ ጎጃም ዞን ፍኖተሰላም ከተማ አስተዳደር ባለፈው 2014 በጀት ዓመት ግንባታቸው የተጀመሩ መሰረተ ልማቶች ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።

 

ፕሮጀክቶቹ በከተማ አስተዳደሩ የውስጥ ገቢ፣ በህብረተሰቡ ተሳትፎና በዓለም ባንክ ድጋፍ ከ140 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ተደርጎባቸው የተገነቡ መሆናቸውን የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ልየው አንሙት ተናግረዋል።

 

ለምረቃ የበቁት መሰረተ ልማቶች የኅብረተሰቡ የረጅም ጊዜ ጥያቄዎች መሆናቸውን የገለጹት ከንቲባው የውሃ ማስፋፊያ፣ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ፣ የመብራት መስመር ዝርጋታ፣ የመስኖ ፕሮጀክት፣ የተፋሰስ ግንባታና ሌሎችንም የሚያጠቃልል መሆኑን አመላክተዋል።

 

የመሠረተ ልማት አውታሮችን በጥራት ለማከናወን ጥረት መደረጉን የገለጹት ከንቲባው በተያዘው 2015 የበጀት ዓመትም የተጀመሩትን ማጠናቀቅና አዲስ ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ ገንብቶ የኅብረተሰቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው ብለዋል።

 

የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መልካሙ ተሾመ ÷በዞኑ የሚገኙ ከተሞችን ማዘመንና ለነዋሪዎች ምቹ ማድረግ የሁሉም አመራር ቀዳሚ ተግባር በመሆኑ የሕዝቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ በትኩረት እየተሠራ ነው ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.